ቀጥታ፡

በቤንች ሸኮ ዞን ያለአግባብ ዋጋ ጨምረውና ምር ት ደብቀው የተገኙ 965 የንግድ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሚዛን አማን፣ መጋቢት 27/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ሦስት ሳምንታት በተደረገ ክትትል ያለአግባብ ዋጋ ጨምረው፣ ምርት ደብቀውና ያለፈቃድ ሲሰሩ የተገኙ 965 የንግድ ቤቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የቤንች ሸኮ ዞን ንግድና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።

 የመምሪያው ኃላፊ አቶ ታምራት ከተማ እንደገለጹት፤ ከተወሰደው እርምጃ መካከል  እንደየጥፋታቸው  ንግድ ቤቶችን  ማሸግና 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቅጣት ይገኝበታል።

"ህዝቡ በኑሮው ውድነት እንዲሰቃይ የሚያባብሱ ማንኛውም ንግድ ቤቶች ላይ በየደረጃው የተዋቀረ ግብረ ኃይል ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል" ብለዋል።

ህብረተሰቡ ህገወጦችን ሲያገኝ አጋልጦ በመስጠት ኑሮን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

በከተማዋ የነዳጅ ማደያ አካባቢ ሆነው  ቤንዚን የሚሸጥባቸው ቤቶችን በማሸግ እየተስተዋለ ያለውን ህገ ወጥነት ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ በበኩላቸው ፤ የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነት ችግር ለማቃለል  ያለመታከት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የንግድና የምርት አቅርቦት ሥርዓትን ከደላሎችና ህገወጦች ለማውጣት  የተዋቀረው ግብረ ኃይል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዋጋ ንረት ችግር በፍጥነት እንዲፈታ የጋራ ጥረትን ስለሚጠይቅ ሸማቹ እና ህጋዊ ነጋዴ ከመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከሚዛን አማን ከተማ ሸማቾች መካከል አቶ ታጠቅ አሰፋ በሰጡት አስተያየት፤ የኑሮ ውድነት በየቀኑ እየጨመረ እያስመረራቸው መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም ለውጥ እየታየ ባለመሆኑ በደንብ መፈተሽ ቢቻል ጥሩ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

የንግድ ቤቶች በህገ ወጥ ዋጋ ጭማሪ ታሽገው ሲከፈቱ የበለጠ ጨምረው ሲሸጡ እንደሚስተዋል ጠቁመው "የሚወሰደው እርምጃ አንድ ጊዜ ብቻ ሆኖ መቆም የለበትም" ብለዋል።

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ውድነሽ በዛብህ፤ የእለት ገቢና የገበያ ዋጋ ሰፊ ልዩነት በማሳየት በኑሯቸው ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን ገልጸዋል።

እቃ ሱቃቸው እያለ የነገን ከፍ ያለ ዋጋ በመጠበቅ የለም የሚሉ ስግብግብ ነጋዴዎች በአካባቢያቸው እየበዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስት ህገወጦችን በመከታተል እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ አጥፊዎችን ለማጋለጥ ዝግጁ መሆናቸውን ተናገረዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም