የነቀምቴ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች አሸባሪውን ሸኔን በፅናት ይታገላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የነቀምቴ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች አሸባሪውን ሸኔን በፅናት ይታገላሉ
ነቀምቴ መጋቢት 27/2014(ኢዜአ) የነቀምቴ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ንጹሃን ዜጎችን በመግደል ሀብት ንብረት በመዝረፍ የሕዝቡን ሰላም እያናጋ ያለውን አሸባሪውን ሸኔን ከመንግሥት ጎን ሆነው እንደሚፋሙት አስታወቁ።
የነቀምቴ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪውን ሸኔ ንጹሃን ዜጎችን በመግደልና በማሰቃየት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ ነው።
የሕዝቡን ደህንነትና ሰላም ለማረጋገጥ በሽብር ቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።
ከመንግሥት ጎን ሆነው እኩይ ዓላማውን ለማምከን አስፈላጊውን መስዕዋትነት ሁሉ እንደሚከፍሉ አስታውቀዋል።
አሸባሪው የሸኔ ዓላማና ግብ የሌለው፤ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክል፤ንጹሃን ዜጎችን በመግደልና በመዝረፍ እያሰቃየ ያለ የሽብርተኞች ስብስብ ቡድን ነው ብለዋል።
ስማቸውን መግለጽ የፈለጉ ነዋሪ እንዳሉት የሽብር ቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ ለማምከን ከመንግሥት ጎን ሆነው በመታገል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሠላም የሁሉም መሠረት መሆኑንና ሠላም ከሌለ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲሁም የሀገር ዕድገት የማይታሰብ መሆኑንም አስረድተዋል።
የሽብር ቡድኑ ግብረ አበሮቹ ጋር በፈጸመው ጥቃት የበርካታ ንጹሃን ዜጎችን ሕይወት ማጥፋቱንና ማፈናቀሉን ተናግረዋል።
በመሆኑም መንግስት ከሚወስደው እርምጃ ጎን ለጎን ህዝቡ ጽንፈኞቹን ለይቶ ከአካባቢው መንቀል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የከተማው 03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ መልካሙ ቡልቲ በበኩላቸው በአካባቢው የፀጥታ ችግር መሰረቱ፣ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክለው አሸባሪው ሸኔ መሆኑን ሕዝቡ በሚገባ መገንዘቡን ተናግረዋል።
የሽበር ቡድኑ በከተማው በርካታ አመራሮችንና የመንግሥት ሠራተኞችን መግደሉን ገልጸው፤ የከተማው ሕዝብ በመተባበር ሸኔን አጋልጦ ለፀጥታ ኃይሉ መስጠት ከአካባቢው በማጽዳት አለበትም ብለዋል።
የከተማው 07 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው አሸባሪው ሸኔ ንጹሃን እየገደለና እየዘረፈ በመሆኑ የሽብር ቡድኑን በፅናት መታገልና ማውገዝ ግዴታችን አድርገን ወስደናል ብለዋል።
የዞኑ የሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረጋሣ ዳባ እንዳሉት በዞኑ ሕዝቡ ከሚሊሻ እና ከመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጋር በመተባበር ሸኔን ለማጽዳት እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ከምን ጊዜውም በላይ በሁሉም አቅጣጫዎች በተቀናጀና በተደራጀ ሁኔታ አመርቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዞኑ የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦሉማ ደሣለኝ በበኩላቸው የዞኑ ሕዝብ ሸኔን እኩይ ዓለማ ለማምከን ከምን ጊዜው በበለጠ በተደራጀ ሁኔታ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
አካባቢውን በመጠብቅ፣ ፍተሻ በማያካሄድ፣ ለፀጥታ አካላት መረጃ በሚሰጠት፣ ስንቅ በማዘጋት ጭምር ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት በሰላም እጃቸውን ከመስጠት ባለፈ የደበቁትንም መሳሪያ አምጥተው ለፀጥታ አካላት እየሰጡ መሆናቸውን በማውሳት።
በመሆኑም ሕዝቡ አሸባሪውን ሸኔን ከአካባቢው በማጥፋት ወደ እርሻው ለመመለስ እያደረገ ያለው እንቅቃሴ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው በለዋል፡፡