የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራ መጠናከር የኢትዮጵያን ማንነት፣ ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ሚናው የጎላ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2014(ኢዜአ) የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራ መጠናከር የኢትዮጵያን ማንነትና፣ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ሚናው የጎላ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሙዚቃ ባለሙያዎች ገለፁ፡፡

ኦርኬስትራ ማለት የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች፤የክር፣የትንፋሽም ሆኑ የምት መሣሪያዎች በአንድ ላይ ተናበው ህብረ ድምፅ በማውጣት መጫወት ወይም የሙዚቃ ቅንብር መፍጠር መቻል ነው።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ በቀዳሚነት የሀገረሰብ ሙዚቃ መሣሪያዎችን ወደ ኦርኬስትራ በመቀየር መሥራት የተጀመረው ቫዮሊን ተጨዋች በሆኑት የሙዚቃ ዜማ ደራሲ እና አቀናባሪ በሻህ ተክለማርያም አማካኝነት ነው።

በመቀጠልም እንደ "ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ" እና "ሕዝብ ለሕዝብ" ያሉት የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራዎች የኢትዮጵያን የኦርኬስተራ ሙዚቃ ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረጉ ናቸው።

በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት መምህርና የሙዚቃ ባለሙያ ኢዩኤል መንግሥቱ የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራ የኢትዮጵያን  ሙዚቃ አጉልቶ ለማሳየት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጿል።

ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከአራት ቴአትር ቤቶች ለተውጣጡ ሙዚቀኞች ባለፉት 10 ቀናት የሰጠው የሙያ ማዳበሪያ ሥልጠና በተለይ ለባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራ መጠናከር መልካም ጅማሮ ነው ብሏል።

ይህም ተዳክሞና ጠፍቶ የነበረው የኢትዮጵያ የኦርኬስትራ ሙዚቃ ዘርፍ መልሶ ለማነቃቃት አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግሯል።

በቀጣይም ሀገር በቀል መሣሪያዎችን በመጠቀም ሙሉ የኦርኬስትራ ቅርፅ በመፍጠር የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራን መሥራት እንደሚቻል  ገልጿል።

ለዚህም ከባህልና ስፖርት ሚኒስትር ጀምሮ ፣ ቴአትር ቤቶች ፣ የትምህርት ተቋማት ፣ ግለሰቦችን ጨምሮ ለዘርፉ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ነው የተናገረው።

በእንጦጦ ፖሌ ቴክኒክ ኮሌጅ መምህርና የሙዚቃ ባለሙያ በላይ ዓለማየሁ በበኩሉ የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራ መጠናከር የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለዓለም ለማስተዋወቅ ይረዳል ነው ያለው።

የባህል ሙዚቀኞችንም በኦርኬስትራ ሙዚቃ ዙሪያ ሥልጠና በመስጠት የሙዚቃ ንድፈ ሀሳቦቻቸውን ማዳበር እንደሚያስፈልግም ገልጿል፡፡

የሙዚቃ ባለሙያ ሠርፀ ፍሬስብሐት፤ የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራ በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ከሚቀናበሩ የኦርኬስትራ ሙዚቃዎች እኩል አቅም እንዳለው ይናገራል፡፡

ለዚህም ቀደም ያሉት የኢትዮጵያ ድምፃውያን በባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅበው ያወጡት ሙዚቃ ትልቅ ማሳያ ነው ብሏል።

አሁን ላይም ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቹን የበለጠ በማዘመንና ትልቅ የባህል ሙዚቃ ኦርኬስትራ በመፍጠር ሙዚቃዎችን አስቀርፆ ለሕዝብ እንዲደርሱ ማድረግ ይቻላል ነው ያለው

ይህ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያን ሙዚቃ አጉልቶ ለማሳየት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም