ኤች አር-6600 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት---የህግ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኤች አር-6600 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት---የህግ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ መጋቢት 27/2014 (ኢዜአ) ኤች አር-6600 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ በሀገር ውስጥና በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያዎች ገለጹ።
የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አዲስ ኤችአር 6600 የተባለ ረቂቅ ሕግ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
በኒው ጀርሲው የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖወስኪ ለአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተዋወቀው ረቂቅ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንደሚኖረው በርካቶች ከወዲሁ እየገለፁ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህ ረቂቅ ህግ በአሜሪካ ኮንግረስ እንዳይጸድቅ ተቃውሞ እያሰማ ይገኛል።
ኢዜአ ረቂቅ ህጉ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ እንዳይሆን ምን ማድረግ ይገባል ሲል የህግ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የግል ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ ረቂቅ ህጉ በአንድ ሉዓላዊ አገር ላይ ጫና ለመፍጠር እየተደረገ ያለ ሙከራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ትክክለኛ ያልሆነ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ረቂቅ ህጉ በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ልማት ላይ ጫና እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት፡፡
በተጨማሪ ረዥም ዘመናትን ባስቆጠረው የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ላይም ራሱን የቻለ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረውም አንስተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ በሀገር ውስጥና በውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ጠብቀው ረቂቅ ህጉን በመቃዎም በጋራ መቆም አለባቸው ነው ያሉት፡፡
በተመሳሳይ ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ ፋሲል ስለሺ፤ ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል።
ይሁን እንጂ እንደዚህ አይነት ጫናዎችን በዘላቂነት መቋቋም የሚቻለው በራስ ኢኮኖሚ አቅም መቆም ሲቻል ብቻ በመሆኑ እዚህ ላይ መትጋት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
በመሆኑም የውስጥ ኢኮኖሚ አቅም ግንባታ ላይ ሁሉም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡