ቀጥታ፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ለመከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2014(ኢዜአ) የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ለመከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ፡፡   

የተለያዩ ተቋማት ለመከላከያ ሰራዊት የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

በዚህም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ የኮሪያ ዘማቾች  ሆስፒታልም ከሰራተኞቹ የሰበሰበውን 130 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

በተመሳሳይ ተስማሚ ቴክኖሎጂ ማዕከል የተሰኘ ተቋም ለሰራዊቱ የሚሆኑ ኮምፒውተሮችና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ በዚሁ ወቅት ድጋፉ ሰራዊቱን ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና ልማት እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ አኳያ ለኢትዮጵያ ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ለሚገኘው ሰራዊት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኀብረተሰቡ የኢትዮጵያን ሰላም ዘላቂ በማድረጉ ሂደት ላይ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ነው ጥሪ ያቀረቡት።    

የተስማሚ ቴክኖሎጂ ማዕከል ተወካይ ዶክተር ታምሩ እውነቱ ማዕከሉ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ለሰራዊቱ በኮምፒውተር ዙሪያ የአሰልጣኞች ሥልጠና ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡          

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው፤ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ዛሬ ካደረጉት ድጋፍ ባሻገር የአንድ ወር ደመወዛቸውን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።      

ለኢትዮጵያ ሰላም ዋጋ እየከፈለ የሚገኘውን ሰራዊት መደገፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም አክለዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም