ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለብሄራዊ ቡድን ቀዳሚ ተመራጭ ስፖርተኞችን እያፈራ ነው

መጋቢት 27/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለወጣት ብሄራዊ ቡድን ቀዳሚ ተመራጭ ስፖርተኞችን እያፈራ መሆኑን የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው ተናገሩ።

አካዳሚው አሁን ላይ በ10 የስፖርት አይነቶች ስልጠና በመስጠት ላይ ሲሆን ለአራት ዓመታት ስልጣናቸውን ከተከታታሉ በኋላ የሚመረቁ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው፤ አካዳሚው በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በተለይም ለወጣት ለብሄራዊ ቡድኖች ቀዳሚ ተመራጭ ስፖርተኞችን እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።

አካዳሚው የ16 ዓመትና ከዛ በታች ያሉ ታዳጊዎችን ተቀብሎ ለአራት ዓመታት በማስልጠን በወጣትነት እድሜያቸው በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ብሄራዊ ቡድን ተቀላቅለው አንዲጫወቱ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

አካዳሚው በሚሰጠው ሰልጠና ተቀዛቅዘው የነበሩ አንዳንድ ስፖርቶች አይነቶች እንደገና ከፍ እንዲሉ እያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ የአትሌቲክስ ስፖርትን ጨምሮ ኢትዮጵያን ከወከሉ ስፖርተኞች መካከል አብዛኛዎቹ በአካዳሚው ሰልጥነው የውጡ በመሆናቸው ውጤቱ እየታየ ነው ብለዋል።

በቶኪዮ ኦሊምፒክ በብቸኝነት በወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያን የወከለው አትሌት ሰሎሞን ቱፋ ከአካዳሚ ያለፈ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አንበሳው በሌሎች የስፖርት አይነቶችም ተስፋ ሰጭ ጅምሮች አሉ ሲሉ ገልጸዋል።

የስፖርት አካዳሚው አገርን የሚወክሉ ስፖርቶችን ከማፍራት ባለፈ የማህበረሰቡን የስፖርት ግንዛቤ የማስፋት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የአካዳሚው ተመራቂ ወጣቶች የተሻለ እውቀትና ክህሎት ይዘው በመውጣት ብቁ ተወዳዳሪ መሆናቸውን በተግባር እያሳዩ ይገኛሉም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከ2006 ዓ.ም እስካሁን 259 ወጣቶችን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለብሄራዊ ቡድን ማስመረጥ ችሏል።

እስካሁን በአለም አቀፍ ውድድሮች 17 ሜዳሊያዎች፤ በአህጉር አቀፍ የውድድር መድረኮች ደግሞ 33 ሜዳሊያዎች በአካዳሚው በሰለጠኑ ተወዳዳሪዎች የተገኙ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በሚል የተቋቋመው አካዳሚው አሁን ላይ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚል ስያሜ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም