የግብዓት እጥረት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዳያደናቅፍ በትኩረት መሰራት አለበት - ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
የግብዓት እጥረት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዳያደናቅፍ በትኩረት መሰራት አለበት - ምክር ቤቱ
ቦንጋ መጋቢት 27/2014 (ኢዜአ) የግብርና ግብዓቶች እጥረት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዳያደናቅፍ ትኩረት እንዲሰጠው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት አባላት አስገነዘቡ።
የምክር ቤቱ አባላት የክልሉ ምክር ቤት አንደኛ መደበኛ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት እንዳሉት የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል።
የምክር ቤቱ አባል አቶ ተረፈ ሲምቡል የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት እጥረት ፈተና እንዳይሆን አፋጣኝ መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል።
"ክልሉ ከቡናና ቅመማ ቅመም ምርቶች ባለፈ የእንስሳት ሀብት ላይ ትኩረት አደርጎ በመስራት ኢኮኖሚውን ማሳደግ ይጠበቅበታል" ብለዋል።
ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ዳዊት ተሰማ በበኩላቸው ለበልግ ወቅት አዝመራ የሚሆን ምርጥ ዘር በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ባለመድረሱ አርሶ አደሩ ችግር ውስጥ መውደቁን ገልጸዋል።
የግበዓት ዋጋ መጨመር ሌላው የዘርፉ ተግዳሮትና አርሶ አደሩን እያስመረረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የገጠማትን የኢኮኖሚ ቀውስ መሻገር የሚቻለው በግብርና ምርቶች ራሷን ስትችል በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ የሚያሳድጉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
"ክልሉ ሰፊ የእርሻ ማሳና የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ከዓመት እስከ ዓመት ዝናብ ያለው ቢሆንም፤ እስካሁን ያሉትን ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚ መቀየር አልቻለም" ብለዋል።
አሁን ላይ ክልሉ ለሀገር የሚተርፍ ምርት ለማምረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው፣ ያልታረሱ ማሳዎችን ማልማትና ኩታ ገጠም እርሻን ማስፋት መጀመሩን ጠቅሰዋል።
ክልሉ ከተዋቀረ በኋላ የምርጥ ዘር እጥረትን ለማቃለል በሁለት የምርጥ ዘር አዘጋጅ ድርጅቶች 700 ሄክታር የበቆሎ ምርጥ ዘር ለማባዛት ታስቦ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።
"እንደ ክልል የአፋር ማዳበሪያ ችግርን ለመፍታት የአፈር ለምነትን የሚጠብቅ ተመጋጋቢ ግብርናን እናለማምዳለን" ሲሉም አመላክተዋል ብለዋል።
''በዘላቂነት እንደ ሀገር የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የሚወሰደውን የመፍትሔ መንገድ እንጠባበቃለን'' ሲሉም አክለዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ የሚታወቅባቸውን የቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ የቅባት እህሎችና እንስሳት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
"እርሻን ከሰው ኃይል በማውጣት በሜካናይዜሽን ለማከናወን እቅድ ይዘን እየሰራን ነው" ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ሆኖ ዘንድሮ መዋቀሩ ይታወሳል።