ሴት ፖለቲከኞች በአገራዊ ምክክሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጁ መሆን አለባቸው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ሴት ፖለቲከኞች በአገራዊ ምክክሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጁ መሆን አለባቸው ተባለ
መጋቢት 27/ 2014 (ኢዜአ) ሴት ፖለቲከኞች በአገራዊ ምክክሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት የጋራ ምክር ቤት አመለከተ።
የጋራ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ነቢዓ መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገራዊ ምክክሩ በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች መፍትሔን ያመጣል ተብሎ ታምኖበታል።
በተለይም ሴት ፖለቲከኞች የማህበረሰቡን ሁኔታና ፍላጎት በቅርበት የመረዳት ክህሎት ያላቸው በመሆኑ ኀብረተሰቡ በምክክሩ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ችግሮች መፈታት ደግሞ የሴቶች ጥያቄዎች እንዲመለሱ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አንስተው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምክክሩ ስኬታማነት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡
በመሆኑም ሴት ፖለቲከኞች ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ያሉ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ለአገራዊ ምክክሩ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ሴት አባላት በበኩላቸው፤ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሴቶች መምሪያ ኃላፊ ለይላ አሊ ፓርቲያቸው አገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዜጎች እጅግ አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን በጽኑ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ፓርቲያቸው አገራዊ ምክክሩን በሚመለከት ከአባላቱ ጋር ውይይት እያደረገ እንደሚገኝና በተለያዩ አካባቢዎች ባሉት ጽህፈት ቤቶች በኩል ሴቶች በአገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማዋቀር የሚጠበቅበትን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አማራ ክልል ቅርንጫፍ ተወካይ የሺወርቅ መለሰም አገራዊ ምክክሩ ህዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
''ምክክሩን እንደ እድል መጠቀም ያስፈልጋል'' ያሉት ወይዘሮ የሺወርቅ፤ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች የአገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነት ተረድተው ተሳታፊ እንዲሆኑ ከወዲሁ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
"የአገራዊ ምክክሩን አስፈላጊነት በመረዳት በኃላፊነት መሳተፍ ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አባል መዲና ሱልጣን ናቸው።
ፓርቲያቸው ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው አጀንዳዎች መካከል የሴቶች ጉዳይ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ አገራዊ ምክክሩ ፓርቲው ለሚያከናውናቸው ተግባራት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ፓርቲው አባላቱንና ከአባላቱ ውጭ ያሉ ሴቶችን በማወያየት ለምክክሩ ዝግጁ የማድረግ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡