በደቡብ ክልል በበጋ መስኖ ልማት ከ210 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል በበጋ መስኖ ልማት ከ210 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል
አዲስ አበባ መጋቢት 27/2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል በዘንድሮ ዓመት በበጋ መስኖ ልማት ከ210 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ ተናገሩ።
በሁሉም አካባቢዎች የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በክልሉ ምርት የማምረት አቅምን በማሳደግ ግብርናውን የማጠናከር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የበጋ መስኖ ልማት በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው ዓመት በበጋ መስኖ ልማት ከ210 ሺህ ሄክታር በላይ በዘር መሸፈኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜም በመስኖ የሚለማ የበጋ ስንዴ በ6 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መልማቱን አስረድተዋል።
የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ በሚመለከትም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከወሰንና ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ ግጭቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
የተለያዩ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች በመሰራታቸው አሁን ላይ እንደ ክልል የተሻለ ሰላማዊ ሁኔታ የሚታይበት ደረጃ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ፣ በተለያየ መንገድ አጀንዳ በመፍጠር ህዝቦችን የሚያጋጩ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመከላከል ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ብዙ መሰራቱንም አብራርተዋል።
የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ጫና እልባት ማበጀት የሚቻለው ቅድሚያ ሰላምን በማጽናት እና ልማት ላይ በማተኮር በመሆኑ በክልሉ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።
በክልሉ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ሲሆኑ 400 ሺህ ወጣቶች ሥራ ለማግኘት መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
በገጠር እና በከተማ በማሰማራት የሥራ እድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻልም ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የሥራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት በተደራጀ ሁኔታ ወደ ሥራ መግባቱንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ክልሉ በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች ያሉበት እንደመሆኑ፤ የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል የማስቻል ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የቱሪዝም ዘረፉን የባህል ማስተዋወቂያ ብሎም ሁነኛ የገቢ ማግኛ ምንጭ እንዲሆን የማስቻል ሥራ እየሰራን እንገኛለንም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።