ከመላው ዓለም በመሰባሰብ ኢድን በጋራ ለማክበር የቀረበው ጥሪ አንድነትና ትብብርን በተግባር የምናሳይበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከመላው ዓለም በመሰባሰብ ኢድን በጋራ ለማክበር የቀረበው ጥሪ አንድነትና ትብብርን በተግባር የምናሳይበት ነው
አዲስ አበባ መጋቢት 27/2014(ኢዜአ) ከመላው ዓለም በመሰባሰብ ኢድን በጋራ ለማክበር የቀረበው ጥሪ አንድነትና ትብብርን በተግባር የምናሳይበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከየትኛውም ዓለም ለዒድ በዓል የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተቀብሎ ለማስተናገድ መዘጋጀቱንም አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ "በታላቁ ወደ ሀገር ቤት ጉዞ ፕሮግራም" የመጡ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ገፅታ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በመጥቀስ አመስግነዋል።
በዘንድሮው የኢድ በዓል አከባበርም በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት በመምጣት ለበዓሉ እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢድን በኢትዮጵያ በታላቅ ሁኔታ ለማክበር በተደረገው ጥሪ ተደስተናል ብለዋል።
በመሆኑም ከየትኛውም ዓለም መጥተው ኢድን አብረውን ለሚያከብሩ ሁሉ ልንቀበላቸው ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከመላው ዓለም በመሰባሰብ ኢድን በጋራ ለማክበር የቀረበው ጥሪ አንድነትና ትብብራችንን በተግባር የምናሳይበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ይሆናልም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ በድርቅና ጦርነት የተጎዱ፣ የተፈናቀሉና በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ በርካታ ወገኖች ስላሉ ተጋግዘን ድጋፍ ለማድረግም ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ቀርቦላቸው በአገራቸው ተገኝተው አብረውን ለማክበር ስለሚገኙ ሁላችንም ደስተኞች ነን ያሉት ደግሞ በምክር ቤቱ የመስጂዶችና የአውቃፍ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ሸህ መሀመድ ሃሚዲን ናቸው።
በዓሉን በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው በመሰባሰብ ማክበራቸው ይበልጥ አንድነትና ወንድማማችነታቸውን የሚያሳዩበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ለበዓሉ ድምቀትና እንግዶችን ለመቀበል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በታላቁ የረመዳን ወር ህዝበ ሙስሊሙ በመረዳዳት፣ በመተጋገዝና በመተዛዘን በፆምና የተራዊህ ሰላት በፅሞና ፈጣሪውን ለመልካም ነገር የሚለመንበት የተለየ ወር መሆኑ ይታወቃል።
1443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ከአንድ ወር በኋላ በመላው ዓለም የሚከበር ይሆናል።