ቀጥታ፡

43 ሚሊዮን ዜጎች የጤና መድህን አገልግሎትን ተጠቃሚ ሆነዋል

መጋቢት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ ለ43 ሚሊዮን ዜጎች የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን አዋጅ  ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በዚህም በረቂቅ አዋጁ ላይ መካተት ያለባቸውን ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት አበበ፤ የማህበረሰብ ጤና መድህን ተግባራዊ ከሆነ አንስቶ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል 78 በመቶ በሚሆኑት ላይ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም 43 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡

በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማና በደቡብ ክልሎች የተሻለ አፈጻጸም እንዳለ ጠቁመው፤ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ያለውን አነስተኛ አፈፃጸም ለማሻሻልም ቀጣይነት ያለው ስራ ይከናወናል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሰሀረላ አብዱላሂ በበኩላቸው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አዋጅ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል የጎላ ሚና  እንዳለው ተናግረዋል፡፡

መንግስት የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል እና የህክምና መሳሪያ ግብዓት አቅርቦትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

መንግስት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አማካኝነት እንደ ካንሰር፣ የልብና የኩላሊት ያሉ ህክምናዎችን ለህብረተሰቡ በቅርበት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም