እየተስፋፋ የመጣውን ህገ-ወጥ የዝሆኖች አደን ለመከላከል ባለድርሻ ተቋማትን ያሳተፈ አሰራር ተዘርግቷል - ኢዜአ አማርኛ
እየተስፋፋ የመጣውን ህገ-ወጥ የዝሆኖች አደን ለመከላከል ባለድርሻ ተቋማትን ያሳተፈ አሰራር ተዘርግቷል
መጋቢት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) እየተስፋፋ የመጣውን ህገ-ወጥ የዝሆኖች አደን ለመከላከል ባለድርሻ ተቋማትን ያሳተፈ አሰራር መዘርጋቱን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ።
በተደራጀ ሕገ-ወጥ አደን ሳቢያ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዝሆኖች ቁጥር እየተመናመነ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል።
በተለይ ዝሆኖች በስፋት በሚገኙባቸው የኦሞ፣ ባቢሌ እና ማጎ ፓርኮች ላይ ህገ-ወጥ ድርጊቱ መባባሱም ነው የተጠቆመው፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዝሆኖችን ከህገ-ወጥ አደን ለመታደግና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በትብብር መስራት ይገባል።
ከዚህ አኳያ ዝሆኖችን ከአደጋ ለመታደግ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊና ቀጠናዊ ትብብሮች መኖራቸውን አንስተው፤ ኢትዮጵያም የዚሁ ትብብር አካል መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተደራጁ ህገ-ወጥ አዳኞች ለዝሆን ጥርስ ንግድ ሲሉ ዝሆኖችን እየገደሉ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ድርጊቱ በእጅጉን ተባብሶ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይ ከህብረተሰቡ፣ ከፍትህ አካላትና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆን በፍተሻ ጣቢያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማካሄድ የመከላከሉን ስራ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ህገ-ወጥ አደን የሚፈጽሙ አካላትን ወደ ህግ የማቅረቡ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ ኀብረተሰቡ ዝሆኖችን ከጥፋት ለመታደግ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩልም በፓርኮች ላይ የሚከሰትን የእሳት አደጋን ቀድሞ መከላከል የሚያስችል ስልት ተነድፎ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
ይህንኑ ስራ ለማገዝ ኀብረተሰቡን ያሳተፈ ግብረ-ሃይል በማቋቋምና የእሳት አደጋ መከላከል ብርጌድ በማደራጀት ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት፡፡
በተለይም የእሳት አደጋ በተደጋጋሚ በሚነሳባቸው የሰሜን ተራሮች፣ ባሌ፣ ሓላይዴጌ፣ ነጭ ሳር እና ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በዱር እንስሳት ሃብት ልማትና ጥበቃ ዙሪያ ያሉ አሰራሮችን፣ ፖሊሲዎችን፣ የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻል እና በመከለስ ዘርፉን የማጠናከር ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ያለው የዝሆኖች ቁጥር ከ2 ሺህ እንደማይበልጥ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ