ቀጥታ፡

ሚኒስቴሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ግንባታ ላይ በትኩረት ይሰራል

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 26/2014 (ኢዜአ) ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ግንባታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱንም የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ብቁ የሰው ሃይል ግንባታ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በስራ ፈጠራ ክህሎት ማሻሻል፣ የሙያ ደህንነትንና ጤንነትን ማረጋገጥና መሰል የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በጋራ እንዲሰሩ ያስችላል፡፡

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚህን ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ልማትን ለማረጋገጥ የሰለጠነና ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግም እንዲሁ፡፡

በመሆኑም ገበያው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት ከተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማዕድን ልማት በርካታ የስራ እድል ከሚፈጠርባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ዘርፉ ያለውን እድል ለመጠቀም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው በአሁኑ ሰዓት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በባህላዊ የማዕድን ልማት ዘርፍ እንደተሰማሩ ተናግረዋል፡፡

ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለማምረት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አንስተው፤ ከዚህ አኳያ ስምምነቱ በዘርፉ ያለውን  ኋላ ቀር የአሰራር ዘዴ በመቀየር ተወዳዳሪ ምርት ለማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ በዘርፉ ያለውን ብቁ የሰው  ሃይል እጥረት ለመፍታት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም