በዳካርና በርሊን በተካሄዱ የውሃና ኢነርጂ ጉባኤዎች የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት መርህ ማስተዋወቅ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዳካርና በርሊን በተካሄዱ የውሃና ኢነርጂ ጉባኤዎች የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት መርህ ማስተዋወቅ ተችሏል
አዲስ አበባ ፣መጋቢት 26/2014 (ኢዜአ) በዳካርና በርሊን በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ጉባኤዎች ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ያላትን በጋራ የመልማት መርህ ማስተዋወቅ መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው 9ኛው የዓለም የውሃ ፎረም እና ጀርመን በርሊን በተካሄደው 8ኛው ኢነርጂ ሽግግር ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ተሳትፎ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።
ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶክተር) በዚህን ወቅት በጉባኤዎቹ ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል የሰጠችውን ትኩረትና በጋራ የመጠቀም መርህ ማስተዋወቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው ፎረም በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተመራው የአመራርና የባለሙያዎች ልዑክ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የውሃ ልማት ስራዎችና የቀጣይ እቅዶች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸውንም ነው ያነሱት፡፡
ከዚህ አኳያ ፎረሙ የኢትዮጵያን በጋራ የመልማት ፍላጎት ለማስገንዘብ እድል የፈጠረ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸው የውሃ ልማት ስራዎች የታችኞችን ተፋሰስ ሀገራት ታሳቢ ያደረጉና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረቱ መሆኑን ማስረዳት እንደተቻለም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም በፎረሙ በአብነት መነሳቱንም ነው ያወሱት፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታከናውናቸውን የልማት ስራዎች በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራ የተከናወነበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በጀርመኗ መዲና በርሊን በተካሄደው የ8ኛው የኢነርጂ ሽግግር ጉባኤ ላይም ኢትዮጵያ ንቁ ተሳትፎ አድርጋ መመለሷን ገልጸዋል።
በፎረሙም ኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ ያላትን ከፍተኛ የመልማት አቅምና ፍላጎት ማሳየት ያስቻለ ስኬታማ ውይይት መከናወኑን አመላክተዋል።
በፎረሙ በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው ያነሱት፡፡
በፎረሙ በተደረገ ገለፃም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ታዳሽ ኃይል ዘርፍ እያከናወነችው ያለው ልማት በጥሩ ምሳሌነት ተነስቷል ነው ያሉት፡፡
በፎረሙ ኢትዮጵያ በኢነርጂው ዘርፍ ያላትን የማልማት ፍላጎት በማስተዋወቅ በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት ግንዛቤ የተፈጠረበት አጋጣሚ እንደነበርም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም አቋሟን በማጎልበት አፍሪካን በኃይል ለማስተሳሰር እያደረገች የምትገኘውን እንቅስቃሴ ማስረዳት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡