ቀጥታ፡

በአሸባሪው ህወሓት የፈረሰው የ"ጨረቲ ድልድይ" የመልሶ ግንባታ ተደርጎለት ለአገልግሎት በቃ

ደሴ፣ መጋቢት 26/2014-(ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ፈርሶ የነበረው የ"ጨረቲ ድልድይ" ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የመልሶ ግንባታ ተደርጎለት ለአገልግሎት በቃ።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሳምሶን ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት፣ አሸባሪው ህወሓት በወረራ ከቆየባቸው አካባቢዎች ሸሽቶ ሲወጣ ሦስት ድልድዮችን አፍርሶ ሄዷል።

በሽብር ቡደኑ ከፈረሱ ድልድዮች መካከል ከጅቡቲ- ሚሌ- ወልድያ በሚወስደው መንገድ ላይ የተገነባው የጨረቲ ድልድይ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ድልድዩ በመሰበሩ መክንያት ከጅቡቲ፣ ሚሌና ጭፍራ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች በኮምቦልቻ ደሴ አድርገው ለመሄድ ተገደው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

 ነዋሪዎችም ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ በተጨማሪነት ስለሚጓዙ ለወጭና ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን አውስተዋል።

ድልድዩ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካለው የጎላ ጠቀሜታ አንጻር መልሶ በፍጥነት ተገንብቶ ሰሞኑን ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ተናግረዋል።

ድልድዩ 88 ሜትር ርዝመት ቢኖረውም በቡድኑ የፈረሰው 45 ሜትሩ ብቻ በመሆኑ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተገጣጣሚ ብረት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመልሶ ግንባታ የተደረገለት መሆኑን  ገልፀዋል።

ለድልድዩ መልሶ ግንባታ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከወልድያ-ቆቦ-መቀሌ በሚወስደው መንገድ ላይ የነበረና በሽብር ቡድኑ የፈረሰ የአልውሃ 50 ሜትር ርዝመት ያለው  ድልድይም ቀደም ብሎ በ17 ሚሊዮን ብር በተገጣጣሚ ብረት ተሰርቶ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አያይዘው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በአሸባሪው ህወሓት ውጫሌ መግቢያ ላይ የፈረሰው ድልድይም በ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እየተገነባ መሆኑን ጠቁመው የድልድዩ ግንባታ ስራ ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የመልሶ ግንባታ ስራው በ10 ቀን ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ድልድዩ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የድልድይ መህንዲስ ኢንጂነር ግርማ ወርቁ በበኩላቸው ድልድዮቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራት ተገንብተው እንዲጠናቀቁ አስተዳደሩ ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ መደረጉን  ገልጸዋል ።

ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የ"ጨረቲ ድልድይም" ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአፋር ክልል ጭፍራ ከተማ ወደ ወልድያ ከተማ ሲያሽከረክር የነበረው ጌታቸው ካሳ በሰጠው አስተያየት እርሱን ጨምሮ አሽከርካሪዎች በድልድዩ መሰበር ምክንያት በደሴ ዙረው ለመጓዝ መገደዳቸውን አስታውሷል።

 የድልድዩ ግንባታ ሥራ ፈጥኖ ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት በመጀመሩ ችግሩ መፈታቱን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አመራሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በቦታው ተገኝተው ድልድዩን ስራ ማስጀመራቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም