የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተደጋጋሚ የሚገኝበትን የኦዲት ግኝት እንዲያስተካክል ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተደጋጋሚ የሚገኝበትን የኦዲት ግኝት እንዲያስተካክል ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ
አዲስ አበባ ፣መጋቢት 26/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተደጋጋሚ የሚገኝበትን የኦዲት ግኝት እንዲያስተካክል የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንስቲትዩቱን የ2012 በጀት ዓመት የዋና ኦዲተር የህጋዊነት ሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ የኦዲት ግኝት ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችና ማስተካከያዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ገምግሟል።
በኦዲት ግኝቱ ጉድለቶችን መነሻ በማድረግ የተወሰዱ ማስተካከያዎችና የእርምት እርምጃዎች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ለተቋሙ ኃላፊዎች ጥያቄዎችን አቅርቧል።
የወጪ ሂሳብን፣ ትክክለኛ የሂሳብ መደቡን ያልጠበቀ ወጪን፣ ያላግባብ የወጣ ወጪን፣ ንብረት አስተዳደርን፣ የተሽከርካሪ አያያዝና አጠቃቀምን በተመለከተ በኦዲት የተገኙ ጉድለቶች ላይ የተወሰዱ ማስተካከያዎችን ጠይቋል።
ያላግባብ የወጣ ወጪን በተመለከተ ከፌደራል የመንግስት ገንዘብ ክፍያ መመሪያ ውጪ በጡረታ፣ በሞትና ሌሎች ምክንያቶች ከሥራ የተለዩ ጡረተኞች ያላግባብ መከፈሉንና ከ963 ሺህ ብር በላይ የወጪ ሰነድ ለኦዲት ሥራ አለመቅረባቸውን የኦዲት ሪፖርቱ አመላክቷል።
ለአገር ውስጥ ሥልጠና፣ ውሎ አበል፣ ለትራንስፖርትና ለምርምር አላቂ እቃዎች በሚል ከ90 ሺህ ብር በላይ ትክክለኛ የሂሳብ መደቡን ያልጠበቀ ወጪ መገኘቱን የኦዲት ግኝቱን ጠቅሶ የተወሰደውን ማስተካከያ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል።
ኢንስቲትዩቱ በ2012 በጀት ዓመት ለመደበኛና ካፒታል በጀት ከ8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ሥራ ላይ ያልዋለ በጀት መኖሩና በንብረት አስተዳደር በርካታ ችግሮች እንዳሉበት በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታመነ ኃይሉ፤ ለተነሱ ጥያቄዎችና በኦዲት ግኝቱ ላይ የተወሰዱ የእርምት እርምጃና ማስተካከያዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፤ በኢንስቲትዩቱ በ2012 በጀት ዓመት የነበሩ የኦዲት ግኝቶች በ2013 በጀት ዓመትም መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዩብ ተካልኝ ተቋሙ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል እያደረገ ያለውን ጥረት በማጠናከር በቀጣይ የውስጥ ኦዲትን እንደ ደጋፊ አካል አድርጎ መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የውስጥ ኦዲትን እንደ አጋር አለማየት በተቋማት ላይ የሚስተዋል ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የውስጥ ኦዲትን እንደ ደጋፊ በማየት እንዲሰሩ በአጽንኦት አንስተዋል።
አገር አሁን ያለችበትን ሁኔታ በመገንዘብ ከግዥና ሌሎች አላግባብ የሚወጡ ወጪዎችን ተቋማት በትኩረት እንዲመለከቱ አሳስበዋል።
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ፤ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ ሪፖርት እስከ ሚያዝያ 15 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲያቀርብ አሳስበዋል።
የኦዲት ግኝቶችንም የቀጣይ 100 ቀናት እቅድ በማድረግ የማሻሻያ ሥራዎችን እንዲያከናውን አቅጣጫ በማስቀመጥ በተደጋጋሚ የሚታዩ የኦዲት ግኝቶችን ለማረም በትኩረት መሥራት አለበት ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሚወገዱ ንብረቶችን የአወጋገድ እቅድ እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያቀርብ ሰብሳቢው አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የተቋሙ ኃላፊዎች ከቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሰጡ አስተያየቶችን እንደ ግብአት በመውሰድ በቀጣይ የኦዲት ግኝቱን ለማስተካከል እንደሚሰሩ አሳስበዋል።