ቀጥታ፡

ባለሃብቶች ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የኑሮ ውድነቱ በዜጎች ላይ የፈጠረውን ጫና ለማቃለል የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው

መጋቢት 26/2014 (ኢዜአ) ባለሃብቶች ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የኑሮ ውድነቱ በዜጎች ላይ የፈጠረውን ጫና ለማቃለል የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ባለሃብቶች ፎረም ፕሬዝዳንት አሸናፊ ሙሴ ገለጹ።

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመጨረ ከመጣው የዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ ዜጎች በከፍተኛ የኑሮ ውድነት ጫና ውስጥ  ይገኛሉ፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት ደግሞ ችግሩን እጅግ እንዳባባሰው ይገለጻል፡፡

መንግስት የዋጋ ንረቱንና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር  በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ ነው የሚገለጸው፡፡

በዚህም የኑሮ ውድነት አሁንም የዜጎች አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

የአዲስ አበባ ባለሃብቶች ፎረም ፕሬዝዳንት አሸናፊ ሙሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሰው ሰራሽ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ግሽበቶች ኢኮኖሚውን እየፈተኑት ይገኛሉ፡፡

ከተፈጥሯዊ ሁኔታዎች መለዋወጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የዋጋ ግሽበትም ለዘርፉ ራሱን የቻለ ፈተና መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች ተደማምረው ዜጎችን ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸውን ጠቅሰው፤ ባለሃብቶች ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የኑሮ ውድነቱ  የፈጠረውን ጫና ለማቃለል የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በተለይ በተወሰኑ ስግብግብ ነጋዴዎች አማካኝነት የሚፈጠር የዋጋ ግሽበት ሊቀጥል እንደማይገባም ነው ያነሱት፡፡

መልካም እሳቤን ይዘው ህዝባቸውንና አገራቸውን እያገዙ ትርፋማ የሆኑ ነጋዴዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በተቃራኒው "ግርግር ላይ ተመስርተው ትርፍ ለማካበት የሚንቀሳቀሱ ነጋዴ መሳይ ወንበዴዎች እየተበራከቱ መጥተዋል" ብለዋል፡፡

በመሆኑም  በህገ-ወጥ መንገድ ትርፍን ለማካበት የሚሰሩ ነጋዴዎችን ወደ መስመር መመለስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ  የአዲስ አበባ ባለሃብቶች ፎረም ቢሮ ህግን አክብረው የሚሰሩ ነጋዴዎችን በመደገፍና ህገ-ወጦችን ደግሞ በመታገል ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አብራርተዋል፡፡

ባለሃብቶች "ወገኖቻችንን ማገዝ አለብን" በሚል መንፈስ የሚሰሩበት ትክክለኛ ወቅት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

መንግስት አገርንና ህዝቡን ያግዛሉ በማለት ልዩ ድጋፍ የተደረገላቸው ባለሃብቶች በምን መልኩ ሥራቸውን እየከወኑ እንዳሉ ክትትል ማድረግ እንዳለበትም ነው የተናገሩት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም