ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው

መጋቢት 26/2014 (ኢዜአ) ሴቶች በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎና ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

ምክር ቤቱ 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን በጉባኤው አባላቱን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሴት የሥራ ኃላፊዎችን ጋብዟል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ነቢአ መሃመድ እንደገለጹት የሴቶችን መሰረታዊ ችግሮች መፍታትን ዓላማ አድርጎ ምክር ቤቱ መቋቋሙን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ በ2013 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን ተከትሎ መቋቋም እንደቻለ ፕሬዝዳንቷ አብራርተዋል።

በምርጫ ከሁሉም ፓርቲዎች 8 ሺህ 955 እጩዎች መከካል 1 ሺህ 985 ብቻ ሴት እጩዎች መደረጋቸው ገልጸው፤ ይህም ኢ-ፍትሃዊ ነው ብለዋል።

ምክር ቤቱ ከ53 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን ፓርቲያቸውን የወከሉ ሴት ፖለቲከኞች ለሴቶች ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በዋናነት ሴቶች ባሉበት የሙያ መስክ የአመራር ሚናቸው እንዲጎለብት ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ሴቶች የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ንብረት የማስተዳደርና የማፍራት መብታቸው እንዲጠበቅ፣ በፖለቲካና በዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ያለ ጫና እንዲሳተፉ ማድረግ ይጠቀሳል።

በዚህ ረገድ ሴት ፖለቲከኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪዎችና ተሰሚዎች እንዲሆኑ ለማድረግ የጋራ ምክር ቤቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል።  

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሙድ፤ ሴት ፖለቲከኞች  ለሴቶች ተጠቃሚነት በጋራ መሰለፋቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል በነበረው ሥርዓት በፓርላማ የሴቶች ተሳትፎ ከሁለት እስከ ሶስት በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት የሴቶች ተሳትፎ 38 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት።

ይህ መሻሻል ሴቶች እድል ከተሰጣቸው በተሻለ መልኩ የመምራትና የማስተዳደር ሃላፊነት መሸከም እንደሚቸሉ የሚያመላክት መሆኑን ገልጸው ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሒክማ ከይረዲን፤ ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውና ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶች አባላት ቁጥር እንዲጨምርና በአመራርነትና በውሳኔ ሰጪነት ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ነው አጽንዖት የሰጡት።

ይህም ሴቶች ፍላጎቶቻቸውና ጥያቄዎቻቸውን አጉልተው እንዲያሰሙና እንዲደራጁ ከማድረጉ ባሻገር ተጽእኖ ፈጣሪ ሴቶችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት።

ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የምክር ቤቱን ሰነድና ያልተሟሉ የሥራ አስፈፃሚዎች ሹመት ማጽደቅ እንዲሁም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም