ቀጥታ፡

በምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው 19 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ግዥ ተፈፅሟል

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው 19 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን 12 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ግዥ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ፤ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያስፈልጉ ግብአቶች መካከል የአፈር ማዳበሪያ ዋነኛው መሆኑን ይናገራሉ።

በ2014/15 የምርት ዘመኑ የኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት 1 ነጥብ 9 ሜትሪክ ቶን ወይም 19 ሚሊየን ኩንታል በመሆኑ የግዥና ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጀማሪያው ዙር 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል (67 በመቶ) ግዥ ተፈጽሞ ወደ አገር ውስጥ እየተጓጓዘ መሆኑን ገልጸዋል።

ሊገዛ ከታቀደው 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ኤን.ፒ.ኤስ እና ኤም.ፒ.ኤስ የአፈር ማዳበሪያ አይነቶች 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ጅቡቲ ወደብ ሲደርስ፣ 3 ሚሊየኑ አገር ውስጥ ገብቷል ብለዋል።

በተያዘው የሚያዝያ ወር ደግሞ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ ሶስት መርከቦች ከሞሮኮ ወደ ጅቡቲ ወደብ እየተጓጓዙ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፈር ማዳበሪያው ማዕከላዊ መጋዘን ከደረሰ በኋላ ክልሎቹ በኅብረት ስራ ማህበራቱ በኩል አርሶ አደሩን ተዳራሽ ያደርጋሉ ነው ያሉት።

የማዳበሪያ አቅርቦቱ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተወሰነ መዘግየት እንዳለው ጠቅሰው፤ እንደ አየር ንብረቱ ቀድመው የሚዘሩ አካባቢዎች በቅድሚያ ግብዓቱ ይቀርብላቸዋል ብለዋል።

ከባለፈው ዓመት ግዥ ተቀማጭ ማዳበሪያ በመኖሩ አሁን ላይ ቀድመው ወደ ዘር ለሚገቡ አካባቢዎች እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

"ወደ ኢትዮጵያ ማዳበሪያ አይገባም" የሚለው ወሬ ፍጹም የተሳሳተ መሆኑን ጠቅሰው በየዕለቱ ከ90 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከጅቡቲ ወደብ የአፈር ማዳበሪያ እያጓጓዙ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርናውን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብዓት አጠቃቀም ቁልፍ ጉዳይ ቢሆንም ከዓለም አቀፍ ገበያው መቃወስ ግምት ውስጥ አስገብቶ ከወትሮው የተለየ ውጤታማነት በሚያረጋግጥ መልኩ በአግባቡ ግብዓት አጠቃቀም መተግበር እንዳለበት ተናግረዋል።

የማዳበሪያ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ የዋጋ ንረት በማሳየቱ ለኢትዮጵያ ጫና እንዳለው አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የፈጸመችው በወርኃ ጥቅምት 2014 ዓ.ም በመሆኑ እንጂ የወቅቱ ዓለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ እየቀረበበት ካለው አሁናዊ ዋጋ ሲነጻጸር እጥፍ ጭማሪ አለው ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ገበያ መጨመር ምክንያቶችም ለአፈር ማዳበሪያ መስሪያ የሚውለውን የፎስፌት ምርት አሜሪካ በመቀነሷ እንዲሁም ሩስያ እና ቻይና ኤክስፖርታቸውን መጠን በመገደባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ችግር አንጻር አርሶ አደሩ እንደ አማራጭ ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንዲጠቀም መክረዋል።

አሁን ላይ መንግስት አቅርቦቱ ሳይቆራረጥ ተደራሽ በማድረግ ላይ ማተኮሩን ገልፀው በተለይም የዝናብ አጥረት ባለባቸው ደረቃማ አካባቢዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያን አዘጋጅቶ እንዲጠቀም እናበረታታለን ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ይህን በመረዳት አርሶ አደሩ ቀደም ብሎ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አርሶ አደሩ እንዲያዘጋጅ ህብረተሰቡን የማነቃቃት ሰራዎች ስለመከናወናቸውም ተናግረዋል።

በከፍተኛ ደረጃ ማዳበሪያ የማይጠይቁ አማራጭ የጥራጥሬ ሰብሎችን የመዝራት አማራጭም ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም