ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ ነሃሴ 30/2010 በኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግልፅና ተዓማኒ እንዲሆን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ምርጫውን ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ከሰው ንክኪና ከመጭበርበር ነፃ ለማድረግ ከመራጮች ምዝገባ እስከ ውጤት ቆጠራ ድረስ በቴክኖሎጂ ታግዞ ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው ቦርዱ የገለፀው። ቀጣይ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደውን ምርጫ ልዩ የሚያደርገው አገር ወስጥ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ ከአገር ውጭ ሆነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩትም ህጋዊ ሆነው ለመመረጥ መዘጋጀታቸው ነው። ይህ ምርጫ በርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ ትኩረት እንደሚያስፈልገው መንግስትም ሲገልፅ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መጪውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድባብ ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ቀጣዩን ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ በማድረግ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲኖር እንደሚሰሩ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ቀጣዩን ምርጫውን ነፃና ፍትሃዊ ለማድረግ ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ ምርጫ ማድረግ መሆኑን ገልጿል። የቦርዱ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ እንደገለፁት ከመራጮች ምዝገባ እስከ ውጤት ቆጠራ ያለውን የምርጫ ሂደት በኤሌክትሮኒክስ በታገዘ መልኩ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት የመረጃ ቋት እንዳለው የገለጹት አቶ ነጋ አሁን ላይ የትኛው ቴክኖሎጂ ለአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ይበጃል የሚለውን ለመለየት ጥናት እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል። አሁን ላይ ከቀረው ጊዜ አንፃር ቀጣዩን ምርጫ ሙሉ በሙሉ በኤሌከትሮኒክስ ለማድረግ ባይቻልም እንኳን እስከተቻለ ድረስ ለማሳካት እየሰሩ መሆኑን አቶ ነጋ ገልፀዋል። ያም ሆኖ ግን በቀጣዩ ምርጫ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ጅማሮ ከታየ 2017 ዓ.ም ለሚደረገው 7ኛ ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሊጂ ማድረግ የሚቻልበት መሰረት የሚጣልበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ አገራዊና ክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች 62 ሲሆኑ ከውጭ የመጡት ከ12 በላይ የፖለቲካ ሀይሎች በቦርዱ ለመመዝገብ ከቦርዱ ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም