ቀጥታ፡

ስፖርት ያልተነካ የኢንቨስትመንትና የሃብት ምንጭ በመሆኑ ሊሰራበት ይገባል - አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው

ባህር ዳር መጋቢት 25/2014 ያልተነካ የኢንቨስትመንትና የሃብት ምንጭ የሆነውን የስፖርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት እንደሚገባ የቀድሞው የኢትዮጵያ የወንዶች የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ የወንዶች የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አቶ ሰውነት ቢሻው በባህር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት "በዓለማችን እንደ ስፖርት ያለ ባጭር ጊዜ ሃብት የሚፈጥር ኢንቨስትመንት የለም" ብለዋል።

በእግር ኳስም ሆነ በሌሎች የስፖርት አይነቶች የሚሳተፉ ስፖርተኞች ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ለኢንቨስትመንትና ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት ተመራጭ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በስፖርት ዘርፍ ተጠቃሚዎች ስፖርተኞች ብቻ ሳይሆኑ አሰልጣኞች፣ የቴክኒክና ሌሎች የቡድን አባላት፣ ቤተሰቦችና ሌሎች ተሳታፊዎች ሁሉ ከሃብቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን በማብራራት እያንዳንዱ የስፖርት ክለብ ከምግብ ማብሰል ጀምሮ የስራ እድል በመፍጠር አሁን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የስፖርት ክለቦች ህጻናት፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ በመስራት የኢትዮጵያን  ስፖርት በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማስፋት እንደሚገባም አመልክተዋል።

በየደረጃው የሚገኘው የመንግስት መስተዳድር፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በዘርፉ በመሰማራት ራሳቸውን ጠቅመው ህዝቡንና አገርን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለባቸው አቶ ሰውነት አስገንዝበዋል።

የባህር ዳር ከነማ ስፖርት ክለብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዳጊዎችና ህጻናት ላይ ትኩረት በማድረግ ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት የአገር ዋልታ መሆን እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

“ክለቦች ዋንጫ በመሻት የስፖርታዊ ስነ-ምግባርን መጣስ የለባቸውም” ያሉት አቶ ሰውነት "ዋናው ትኩረታቸው የሰው ሃይል ልማት መሆን አለበት" ብለዋል።

ከህጻንነት ጀምሮ በሰው ሃይል ልማት ትኩረት በማድረግ መስራት ከተቻለ ዋንጫም ሆነ ሌሎች የሚያስቡትን ሁሉ ማሳካት እንደሚቻል አብራርተዋል።

ጠንካራ፣ አሸናፊነትን የተላበሰ፣ አምራች፣ ለሀገርና ህዝብ የሚቆረቆር ዜጋ ማፍራት የሚቻለው ወጣቱን ትውልድ በስፖርት ማነጽ ሲቻል እንደሆነም አስረድተዋል።

የባህርዳር ከከነማ ስፖርት ክለብ ፍቅርን፣ ሰላምና አንድነትን በሜዳ ላይ በመስበክ አሁን የሚስተዋሉ ችግሮችን እርስ በእርስ በመተሳሰብ ለመፍታት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በእለቱ የቅዱስ ጊዮርጊስና ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ተገኝተው አብሮነትና መደጋገፍ ላይ ያተኮረ መልዕክት አስተላልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም