ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ግብርና ለማሸጋገር የዘርፉ ተቋማት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል

መጋቢት 25 2014(ኢዜአ) በህዝብ ቁጥር ዕድገት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በግብዓት እጥረት መልከ ብዙ ፈተናዎች የተደቀነበትን የኢትዮጵያን ግብርና ለማሸጋገር የዘርፉ ተቋማት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መሰራት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ።

የግብርና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተሮችን በተመለከተ አገራዊ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን በዚህ ወቅት ከአራት ዓመታት በፊት በሰብል፣ በእንስሳትና አበባ ልማት በክላስተር መሰራት መጀመሩ በዘርፉ ዕውቀትና ክህሎትን ለማሳደግ አስችሏል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 2030 በግብርና ዘርፍ ሁለንተናዊ የሽግግር ግቦችን በማስቀመጥ ለኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፉ በቂ ምርት ማቅረብ የሚያስችል ዕቅድ መንደፏን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ በአምስት  ክልሎች ወደ 430 ሺህ  ሄክታር መሬት በክላስተር እርሻ እየለማ መሆኑን ገልፀው፣ በዚህም ዘርፉ  የኢትዮጵያ የልማት ሕልውና መሆኑ የታየበት እንደሆነም አስታውቀዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ ውስጣዊ ግጭትና ዓለም አቀፍ ጫናዎች ቢኖሩም ችግሩን በመቋቋም የተሻለ ስራ ማከናወን መቻሉን አንስተው ''ዘርፉ የሕልውናችን ምሰሶ ከመሆኑ ባሻገር ከፊታችን የተደቀኑ ተገማችና ኢ-ተገማች ፈተናዎችን ታሳቢ በማድረግ ግብርናው ላይ በልዩ ሁኔታ መስራት ይጠይቃል'' ብለዋል።

በበልግ፣ በመስኖና በመኸር ወቅት የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ  ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የግብርናው ዘርፍ በ5 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ቢኖረውም በየዓመቱ በ2 ነጥብ 5 እድገት በሚያሳየው  የሕዝብ ብዛት የተነሳ አለመመጣጠን እንደሚፈጠር አንስተዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ግብርና በአየር ንብረት ለውጥና በግብዓት አቅርቦት ችግሮች ተፈትኗል ያሉት ዶክተር ይፍሩ፤ በዚህም በአየር ንብረት ለውጥና የህዝብ ቁጥር መጨመር ላይ ስትራቴጂካዊ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየ10 ዓመቱ በሁለት በመቶ የሙቀት መጨመር እንደሚገጥምና በኢትጵያም ደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በዚሁ የተነሳ 20 በመቶ ዝናብ በመቀነሱ ዘርፉ ፈተና እየገጠመው ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የግብዓት እና የተሻሻለ ምርጥ ዘር ምርቶቹ ከውጭ የሚገቡ በመሆናቸው የዋጋ ንረት እንደሚያጋጥም አመልክተው ምርቱን በሐገር ውስጥ ማምረት የሚጀመርበት እድል ቢኖር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል።

በምርምር የፈለቁ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶ አደሩ በማዳረስ ብቻ 20 በመቶ ምርትን ማሳደግ ስለሚቻል የግሉን ተዋናዮች በዘርፉ ማሳተፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ግብርናው መሸከም የማይችለው ህዝብ ደግሞ ወደ የኢንዱስትሪውና አገልግሎት ዘርፍ እንዲገባ ማስቻል እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

የግሉን ዘርፍ ወደ ምርጥ ዘር ማባዛት ስራ እንዲሳተፍ የሚያደርግ የህግ ማዕቀፍ ማሻሸያ እየተደረገ በመሆኑም ዘርፉ ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ፣ በፋይናንስና በግብርና አመራር የሚታዩ ማነቆዎችን መፍታት፣ ሰፋፊ እርሻን ማሳደግ፤ የህብረት ስራ ማህበራትን ማጠናከር ፣ የድሕረ ምርት ብክነትን መቀነስ በሚሉ ሐሳቦች ላይ በመድረኩ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም