ወጣቶች ማኅበራዊ ሀብቶችን በመጠቀም የህዝቦችን ትስስር ሊያጠናክሩ ይገባል- አቶ ታዬ ደንደዓ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ማኅበራዊ ሀብቶችን በመጠቀም የህዝቦችን ትስስር ሊያጠናክሩ ይገባል- አቶ ታዬ ደንደዓ
ሆሳዕና መጋቢት 25/2014(ኢዜአ) ወጣቶች ለልዩነት ምክንያት ከሚሆኑ አመለካከቶች ይልቅ ማኅበራዊ ሀብቶችን በመጠቀም የህዝቦችን ትስስር ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ አመለከቱ፡፡
"ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና" በሚል መርህ የወጣቶች የውይይት መድረክ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ወጣቶች በማህበረሰብ ውስጥ ያሉ እሴቶችን በማጠናከር አዎንታዊ ሰላም ለመፍጠር ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የመሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ወደ ልማት በመቀየርና እድገት ለማስመዝገብ አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተው ለተግባራዊነቱም ቀደምት አባቶቻችንን ያቆዩልንን የኖረውንና የምንታወቅበትን የማህበራዊ እሴቶቻችንን መጠበቅና ማስቀጠል ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ወጣቶች ለሰላም፣ ለመቻቻልና ለአብሮነት መጠናከር ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበውም በሀገሪቱ ላይ የተጋረጡ ፈተናዎችን ለመሻገር ማህበራዊ ዕሴቶቻችን ያላቸውን ሚና በአግባቡ መረዳትና መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የዋቸሞ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው ማህበራዊ ሀብቶቻችንን ለሰላም ግንባታ በመጠቀም ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረት ዜጋ መፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።
የቀደምት እሴቶቻችንን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰጠ ያለው ትኩረት መቻቻልን፣ መከባበርና መረዳዳትን እንዲሁም ሀገር በቀል ሀብቶች ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት መሠረት የሚጥል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
"ወጣቶች ማህበራዊ ሀብቶችን በተገቢዉ መንገድ በመጠቀም ለሚገጥሟቸዉ ችግሮች መፍትሄ አምጪ በመሆን በዜጎች መካከል ያለው ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር የማድረግ ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል" ሲሉ ሚኒስቴር ዴኤታው አስገንዝበዋል ፡፡
በመድረኩ ተሳታፊ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ወጣት ምንተስኖት ጴጥሮስ እንደተናገረው ወጣቱ ትውልድ በሀገሪቱ ዘላቂና ጠንካራ ሰላም እንዲረጋገጥ ቀዳሚ ተዋናይ መሆን አለበት፡፡
“ወጣቶችን ማህበራዊ ሀብቶቻችንን ተጠንቅቀን በመያዝና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ያለንን እምቅ አቅምና ጉልበት በተቀናጀ መልኩ ለሀገር እድገትና ለውጥ መጠቀም ከቻልን ቀዳሚ ተጠቃሚዎች የምንሆነው እኛው ነን” ብሏል፡፡
"ትውልዱ በማያውቃቸው ተገቢነት የሌላቸው ትርክቶችን በምክንያት በመሞገትና ለአፍራሽ አጀንዳዎች ባለመገዛት ምክንያታዊ ትውልድ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል" ሲል አክሏል ፡፡
’’ለሀገርም ይሁን ለትውልድ ጥቅም በሌለው ጽንፈኛ አመለካከት ላይ ተመርኩዘን ጊዜያችንና ጉልበታችንን ከማጥፋት ይልቅ ሀገርን አንድ እርምጃ ሊያሳድግ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መስራት አለብን’’ ያለዉ ደግሞ ወጣት ዳዊት ተስፋዬ ነው፡፡
"ለልዩነትና ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች ሲፈጠሩ ከአባቶች በወረስናቸው የአብሮነት እሴቶች ልንፈታ ይገባል " ሲልም አመልክቷል።