የአፍሪካ ቀንድ አብሮነት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቀንድ አብሮነት
በሰለሞን ተሰራ
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ጥንታዊ ሀገሮች አንዷ ከመሆኗም በላይ ከአውሮፓውያኑ ቅኝ ግዛት ራሷን በመከላከል ነፃነቷን ጠብቃ ቆይታለች። የአገሪቷ መሪዎች የተከተሉት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ነፃነት ለመጠበቅ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በባህል፣ በታሪክ፣ በአብሮ መኖር፣ በመዋለድና አንዱ የሌላኛውን ሀገር እንደ ሁለተኛ መኖሪያው በመቁጠር የቅርብ ግንኙነት አዳብረዋል።
ኢትዮጵያ የሀገራቱ የጋራ እድገት ሁሉንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በመገንዘብ ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድን ባለመከተል፣ ለውስጥ ችግሮቿ ቀዳሚ ትኩረት በመስጠት ልማቷን ለማፋጠን እየተጋች ትገኛለች።
በዚህም ድህነት በተሰኘው አሳፋሪ ጠላቷ ላይ የህዝቦቿን ጠንካራ ክንድ በማስተባበር የቀጣናው ብሎም የአህጉሪቱ የልማት እመርታ ተምሳሌት በመሆን እየተጓዘች ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክም በአዲስ ገፅታ መታየት በመጀመሯ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል።
ኢትዮጵያ የኢጋድ አባል አገራት ለቀይ ባህር ቀረቤታ ያላቸውና ምናልባትም ባካባቢው ሊከሰት የሚችል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሊጎዳቸው ወይም ሊነካቸው የሚችል መሆኑን በሚገባ ተገንዝባለች፡፡
ኤርትራ፡ ሱዳን፡ ጂቡቲና ሶማሊያ ወይም ሶማሊላንድ የቀይ ባህር አጎራባች አገራት ሲሆኑ ሌሎቹ አባል ሀገሮችም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው ከቀይ ባህር ጋር የተቆራኘ ነው፡፡
ለምሳሌ የኢትዮጵያ 90% የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ የሚተላለፈው በቀይ ባህር በኩል ሲሆን ደቡብ ሱዳን፡ ኬንያና ኡጋንዳም ቢሆኑ የንግድ እንቅስቃሴያቸው በዚሁ ባህር ላይ የሚተላለፍ ነው፡፡
ስለሆነም በቀይ ባህር የሚደረግ ማንኛውንም ፖለቲካዊ፡ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የኢጋድ አባል አገራትን ጥቅም የሚነካ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ይህን ወሳኝ እውነታ የተረዳችው ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎቿ የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጋለች ።
የህዳሴ ግድብ
የህዳሴው ግድብ ለታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ከኢትዮጵያ ያልተናነሰ ጥቅም የሚያስገኝላቸው ሲሆን ወንዙ ዓመቱን ሙሉ ተመጣጣኝ የውኃ ፍሰት እንዲኖራቸው ያደርጋል እንዲሁም ግድቦቻቸውን ከደለል ይከላከላል።
የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለሀገራቱ ከሚሰጠው ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም ባሻገር በሱዳኑ ጀበል አወሊያ ግድብና በግብጹ አስዋን ግድብ ላይ በትነት የሚባክነውን የውኃ መጠን ይቀንሳል።
እነዚህ ግድብች ያሉበት ቦታ የህዳሴው ግድብ ካለበት ሥፍራ አንጻር እጅግ ሞቃታማ በመሆኑ እንዲሁም ጀበል አወሊያም ይሁን አስዋን ሜዳ ላይ የተገነቡ በመሆናቸው ለከፍተኛ ትነት የተጋለጡ ናቸው።
በአንጻሩ የህዳሴው ግድብ በአነስተኛ ቦታ ላይ ከፍተኛ የውኃ ክምችት የሚይዝ በመሆኑ ለትነት የተጋለጠ አይደለም።
የህዳሴ ግድቡ ለሀገራቱ ከሚሰጠው ጠቀሜታ አኳያ አንዳንድ የውኃ ባለሙያዎች እንደሚሉት በላይኞቹ የናይል ተፋሰስ አገራት የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በስፋት ካልተሰራ የወንዙ ውኃ አደጋ ላይ ሊወድቅ ስለሚችል መተባበሩ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ።
በመሆኑም የወንዙን ዘላቂ ጥቅም የሚፈልግ ሁሉ ለወንዙ ቀጣይ ሁኔታ ማሰብ ግድ ስለሚለው ኢትዮጵያ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ ቀደም በመረዳቷ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በመጀመር በስፋት ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡
ለአካባቢ ጥበቃ ስኬቱ ኢትዮጵያ መርኃ ገብሩን ወደ ጎረቤት ሀገራት ለማስፋፋት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች ነው፡፡
የኃይል አቅርቦት ትስስር
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግብፅና ሱዳን በተመጣጣኝ ዋጋ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ሲሆን ፣ግድቡ የወንዙን ሥነ ምህዳራዊ ሁኔታ መጠበቅ ስለሚችል በየወቅቱ የሚዋዥቀውን የወንዙን የውኃ መጠን በማስተካከል ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ፍሰት እንዲኖረው ያደርጋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት በተመጣጣኝ ዋጋ ከምታቀርበው የኃይል አቅርቦት የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላታል።
ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብን ለኃይል ልማት እንጂ ለመስኖ ልማት እንደማታውለው በተደጋጋሚ በማሳወቅ ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ እንስራ እያለች ጥሪ ማቅረቧን አሁንም አላቋረጠችም።
በመሠረቱ ኢትዮጵያ እንደሱዳን ሰፊ የመስኖ መሬት የሌላት ከመሆኑም በላይ የግድቡ ሥፍራ ወደ ሱዳን ጠረፍ የተጠጋ በመሆኑ ለመስኖ ሥራ ብዙም የሚያገለግል አይደለም።
ኢትዮጵያ ካላይ የኃይል አቅርቦት ላይ ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያን፣ሱዳንንና ደቡብ ሱዳንን የኤሌክትሪክ ኃይል እንድትጠቀም ለማድረግ እየጣረች ነው።
የኢኮኖሚና መሰረተ ልማት ግንባታ
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በፈጣን ሁኔታ ማደግ ከጀመረ አንስቶ ከጎረቤት አገራት ጋር በፖለቲካ፣ በንግድ፣ በባህል፣ በሠላም ማስከበር ያላትን ትስስር እያጠናከረች ትገኛለች።
ኢትዮጵያና ጅቡቲ እጅግ የጠነከረ ግንኙነት በመፍጠር ዛሬ ላይ አንዷ አገር ለሌላኛዋ የህልውና ምንጭ እስከመሆን መድረሳቸውን መመልከት ይቻላል።
ጅቡቲ የባህር በሯን ለኢትዮጵያ በማከራየት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ስታገኝ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን ለጅቡቲ በማቅረብ ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት ችላለች።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ አማካኝነት የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው።
በዚህም በመሠረተ ልማት ግንባታና በንግድ በርካታ አስተዋፅኦዎችን ያደረገች ሲሆን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብም ከቀጠናው ቀዳሚም መሆን ችላለች።
በቀጣናው ሀገራት ውስጥ የጋራ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትም እየሰራች ሲሆን ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ጋር የመንገድ ግንኙነት በመፍጠር ለጋራ ተጠቃሚነት በመትጋት ላይ ትገኛለች።
በዚህም ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ዘርግታለች። ከኬንያ ጋር የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታ መስመርንም እያሳለጠች ነው።
ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ የአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣ የኃይል አቅርቦት በማካሄድ የህዝቦች ግንኙነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ጥረቷን ቀጥላለች።
ሰላም ማስከበር
ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሰላም፣ ፀጥታና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ባለችው ሚና በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት አልባነትና አክራሪነት በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች።
እርግጥ ሰላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለፀገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመስራት ላይ ትገኛለች።
ሰላም መርሁ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት አፍሪካዊ አስተዋፅኦውንና ኃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል፤ ዛሬም ድረስ እየተወጣ ነው።
በዚህ መሰረትም በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሠላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንድትሆን አስችሏል።
ላይቤሪያም ባለፉት የአውሮፓውያን አስርት መጨረሻ ዓመታት ላይ በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሀገሪቱን ወደ ሠላምና መረጋጋት ጎዳና ለመመለስ በተደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሳትፎ ወደር አልነበረውም።
ሰላም አስከባሪ ኃይሉ በሀገሪቱ ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግም የላቀ ሚናውን በመወጣቱ የክብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በሱዳን-ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሰላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ አሻራዋን ማሳረፏ ይታወቃል።
ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም ብቻውን የተሰማራ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ስር በማሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባር አከናውናለች።
ይህ ተግባሯም ኢትዮጵያ በሁለቱም ሀገሮች መንግሥታትና ህዝቦች አክብሮት እንዲቸራት አድርጓል።
በጎረቤት ሶማሊያም አቆጥቁጦ የነበረውን የፅንፈኝነትና የአክራሪነት ተግባሮችን በመዋጋት ዛሬ በዚያች ሀገር ፌዴራላዊ መንግስት እንዲመሰረት የበኩሏን እገዛ አድርጋለች።
ከአሚሶም ውጭም ባለው ሰራዊቷ አማካኝነት በሶማሊያ ህዝብ ይሁንታ የተመረጠውን አዲሱን የሀገሪቱን መንግስት እየደገፈች ትገኛለች።
መውጫ
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በመሰረተ-ልማት፣ በንግድ፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በተፈጥሮ ሃብት፣ በመልክዐ ምድርና በሃይማኖት የተሳሰረች መሆኗን በመገንዘብ ይህንኑ የትስስር ገመድ በመጠቀም ከቀጠናው አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በማዳበር ላይ ትገኛለች።
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያንና ጅቡቲን የሚያገኛኝ የባቡር ሃዲድ ገንብታለች፣ ኢትዮጵያንና ሱዳንን እንዲሁም ኢትዮጵያንና ኬንያን የሚያገናኝ የየብስ ትራንፖርት ግንባታን እያፋጠነች ትገኛለች።
በርበራ-አዲስ አበባ ኮሪደርን እውን በማድረግ ሶማሊያ-ላንድን ከኢትዮጵያ ጋር ለማገናኘትም እየተሰራ ነው።
ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያገናኝ መንገድ ለመገንባት ሁለቱ አገራት ተስማምተዋል በተጨማሪም ጁባን ከአዲስ አበባ ጋር ለማገናኘት የሚያስችል ፕሮጀክት በኢጋድ አስተባባሪነት እየተዘጋጀ ነው።
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን ኤሌክትሪክ ትሸጣለች፣ ለጅቡቲ የመጠጥ ውኃ የምታቀርብ ሲሆን ከጅቡቲና በቅርቡ ከሱዳን የወደብ አገልግሎት እና ከሱዳን ደግሞ የነዳጅ አቅርቦትን ትገዛለች።
ይህ ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር በየነ-ጥገኝነትን በማስፈን አንዱ ካላንዱ መኖር እንደማይቻል እና የጋራ ተጠቃሚነት ዋነኛው የዲፕሎማሲያችን መርህ መሆኑን በተግባር ማሳየት ችሏል።
ኢትዮጵያ በቀጠናው እያስመዘገበች ያለው የልማት እመርታ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በዙሪያዋ ያሉት ጎረቤቶቿም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠንካራ አካባቢያዊ ትብብርና የዲፕሎማሲ ቁርኝት ፈጥራለች።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ ያካበተቻቸውን ተጨባጭ ተሞክሮዎች በመቀመር የመሪነት ሚናዋን በተገቢው ሁኔታ እየተወጣች ትገኛለች።
ይህን ተከትሎ በራሷም ሆነ በአካባቢው ሀገራት የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ የሰላምና የትብብር አድማስ በዲፕሎማሲ ታጅቦ እንዲሰፋ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።