በአገሪቱ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለሚበልጡ ህፃናት የፀረ አምስት ክትባት አገልግሎት በነፃ ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቱ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለሚበልጡ ህፃናት የፀረ አምስት ክትባት አገልግሎት በነፃ ተሰጥቷል
አዳማ ነሀሴ 30/2010 በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ለሚበልጡ ህጻናት የፀረ አምስት ክትባት አገልግሎት በነፃ መስጠቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሀገር አቀፍ የእናቶችና ህጻናት ጤናና የሥርዓት ምግብ አገልግሎት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በሚኒስቴሩ የብሔራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሙላት ንጉስ እንደገለጹት በመጠናቀቅ ላይ ባለው ዓመት የክትባት አገልግሎቱ የተሰጠው በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙና እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ለሆኑ ጨቅላ ህፃናት ነው። የክትባት አገልግሎት ህጻናትን ከህመም፣ ከአካል ጉዳትና ከሞት ለመከላከል ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ መሆኑን አመልክተዋል። በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህፃናት ጤና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ቢራራ መለስ በበኩላቸው የክትባት አገልግሎቱን ለማስፈጸም 790 ሺህ ዶዝ መድኃኒትና 45 ሚሊዮን ብር ለክልሎች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል። “በተለይ የኩፍኝ በሽታ ህፃናትን ለህመም፣ ለአካል ጉዳትና ሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች አንዱና ዋነኛው ነው'' ያሉት ተወካዩ በሽታውን ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተመረጡ 51 ዞኖች የኩፍኝ በሽታን ለመከላከል በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው አጠቃላይ የጨቅላ ህጻናት ክትባት አገልግሎት ሽፋን 96 በመቶ መድረሱንም አመላክተዋል። በዚህ ዓመት በእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት እንቅስቃሴም በመውለድ የእድሜ ክልል ከሚገኙት እድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሆኑ ሴቶች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው “የህጻናትን ጤና ከማሻሻልና የሞት ምጣኔን ከመቀነስ አኳያ ብዙ ርቀት ተጉዘናል'' ብለዋል። የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል 6 ሺህ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የክትባት ማቀዝቀዣ ፍሪጆች ተሰራጭተው ተከላው እየተገባደደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታትም ተመሳሳይ ማቀዝቀዣዎችን ለማሰራጨት መታቀዱን ዶክተር ከበደ ገልጸው ክልሎች መሳሪያዎቹን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል። በ2009 ዓ.ም የጤና መረጃ ሥርዓት መሠረት የጸረ አምስት ክትባት 97 በመቶ፣ የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት 93 በመቶ እንዲሁም ሁሉንም የክትባት ዓይነቶች ያገኙ ሕጻናት ሽፋን ደግሞ 91 በመቶ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሽፋኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ጥሩ ቢሆንም አፈፃፀሙ ግን ከክልል ክልል የተለያየ ነው። ለሶስት ቀናት በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አካላት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።