ቀጥታ፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ዋና መንገድ አካል የሆነው የአዳማ - አዋሽ መንገድ ጥገና እየተደረገለት ነው

አዲስ አበባ  ፣ መጋቢት 24/2014(ኢዜአ) የኢትዮ-ጅቡቲ መተላለፊያ መስመር አካል የሆነው የአዳማ - አዋሽ 60 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ከ816 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከባድ ጥገና እየተደረገለት መሆኑ ተገለጸ።

ጥገናውን 'ዮንአብ ኮንስትራክሽን' የተሰኘ ሀገር በቀል ተቋራጭ የግንባታ ኮንትራት ወስዶ እ.ኤ.አ. ከየካቲት 23 ቀን 2022 ዓ.ም ጀምሮ ጥገናውን በማከናወን ላይ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ እና ቦሰት ወረዳዎች የሚገኘው እንዲሁም ዲቤ ሶሎቄና ወለንጪቲ ቀበሌዎች የሚያገናኘው የመንገድ ጥገና ስራ የኢዜአ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል።

ከ816 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚጠገነው ይህ መንገድ ወጪው ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው ተብሏል።

በ60 ኪሎ ሜትር ላይ የሚከናወነው ከባድ ጥገና ስፋቱ በገጠር 7 ሜትርና በከተማ 14 ሜትር ሲሆን በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።

'ዮንአብ ኮንስትራክሽን' ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅና የግንባታ መሳሪያዎች ኃላፊ የሆኑት ኢንጂነር ተስፋገብርኤል ታደሰ፤ መንገዱ የኢትዮ-ጅቡቲ መተላለፊያና ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍሰት ያለበት ነው።

መንገዱ ለከፍተኛ ብልሽት በመዳረጉና ለትራፊክ ፍሰቱ ምቹ ባለመሆኑ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ጫና ሲያደርስ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ጥገና ሂደቱ በተያዘለት ጊዜና በጀት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ለመንገድ ጥገናው ግብዓት የሚሆኑ የጠጠርና ሌሎች ጥሬ እቃዎች የማምረት ስራ በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው የጥገና ሂደቱ በተሻለ አፈፃጸም ላይ እንዳለ አንስተዋል።

በጥገና ስራው 'በለስ አማካሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር' በአማካሪነት እየተሳተፈ መሆኑ ተጠቅሷል።

የማህበሩ የማቴሪያል መሃንዲስ አብዩ ቢተው እንደሚሉት፣ ጥልቅ የመሬት ምርምር በማካሄድ ጥራት ያለው ስራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው።

በ'ዮንአብ ኮንስትራክሽን' ድርጅት የአዳማ አዋሽ የመንገድ ጥገና ማናጀር ኢንጂነር ቴዎድሮስ ስጦታው በበኩላቸው ከአዳማ-አዋሽ እየተከናወነ ያለው የመንገድ ጥገና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የመንገዱ ብልሽት ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቁ የመኪና እቃዎችን በመስበርና ለብልሽት በመዳረግ ላልተፈለገ የጊዜ፣ የሃብት ብክነትና ለጤና ችግር እየዳረጋቸው እንደሆነ አሽከርካሪዎች ተናግረዋል።

የመንገዱ ጥገና መካሄዱም በጉዞ ሂደት የሚያጋጥማቸውን አስቸጋሪ ውጣ ውረድ በማስወገድ በሰዓቱ ለመግባትና የንብረታቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚረዳቸው አመላክተዋል። 

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ እንደሚያሳየው ግንባታው ሲጠናቀቅም በአካባቢው የሚመረቱ የአትክልት፣ ፍራፍሬና የአዝርዕት ምርቶች የተሻለ ገበያ እንዲያገኙ ይረዳል።

ጥገናው የቱሪዝም መዳረሻ የሆነውን የአዋሽ ብሔራዊ ፖርክ ለጎብኝዎች ምቹ ከማድረጉ ባሻገር ለሀገሪቱ ገቢና ወጪ ምርቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም