ቀጥታ፡

በመጅሊስ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ የተደረገው ውይይት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ በስኬት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 24/2014(ኢዜአ) በመጅሊስ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ የተደረገው ውይይት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።

በመጅሊሱ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ለአንድ ሳምንት ሲያካሂድ የቆየውን ውይይት በማስመልከት የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ መግለጫ ሰጥተዋል።

በውይይቱ 23 ዑለማዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰው በጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር በማድረግ የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በውይይቱ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የክልል ዑለማ ተወካዮችና ከመጅሊስ ውጪ ያሉ ዑለማዎች እንዲወያዩበት ይደረጋል ብለዋል።

የዳዒ ተወካዮች፣ ወጣቶችና ሴቶች ጭምር በውይይቱ እንዲሳተፉ የሚደረግ መሆኑንም የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል።

ከረመዳን ፆም በኋላ ውይይቱ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰው ከውይይቱ ቀጥሎ አስመራጭ ኮሚቴ በማቋቋም የመጅሊስ አባላት ምርጫ ይካሄዳል ብለዋል።

በዚህም ለአንድነትና ለሰላም የሚሰሩ ተወካዮች መጅሊሳቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲረከቡ ይደረጋል ነው ያሉት።

"ሰላምና አንድነት ለሁላችንም ይበጃል" ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ፤ ህዝበ ሙስሊሙ በመካከላችን ልዩነት አለመኖሩን ሊያውቀው ይገባል ብለዋል።

ታላቁን የረመዳን ፆም በፍቅር፣ በእዝነት እና አብሮነት በመፆም ለማሳለፍ ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም