የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የመውጫ ፈተና ሊወስዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የመውጫ ፈተና ሊወስዱ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከሁሉም የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ የሚደረግ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በመውጫ ፈተናው አስፈላጊነት፣ የፈተና አወጣጥና አፈታተን ዝግጅት፣ በአጠቃላይ የትግበራ ሂደት እና ሊያመጣ በሚችለው ውጤት ዙሪያ ከተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች ጋር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምክክር ተደርጓል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጠንካራ ትግበራና ርምጃዎች የሚወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ጥራትን ይደግፋል ተብሎ የታመነበት ስርዓተ-ትምህርትን መሰረት ያደረገ የመውጫ ፈተና አንዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የመውጫ ፈተናው ከሁሉም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎች በተማሩባቸውና በሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም የመውጫ ፈተና ስትራቴጂ የማዘጋጀት እና ስትራቴጂውን የማስተግበሪያ መመሪያ የተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።
የመውጫ ፈተናው የሚዘጋጀው፣ የሚተገበረው እና የሚተዳደረው በዩኒቨርሲቲዎች መሆኑን ገልጸው ለዚህም ትግበራ ፖሊሲና ዝርዝር ማስፈፀሚያ መመሪያ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
በዚህ ረገድ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተመራቂዎች የመውጫ ፈተናውን እንዲወስዱ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ሂደት በህግና በህክምና ሙያ የሚሰጠው የመውጫ ፈተና እና የብቃት ማረጋገጫ ፍተሻ እንደ ልምድ ይወሰዳልም ነው የተባለው።
የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ፕሬዚዳንት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ የመውጫ ፈተናው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ የስራ ገበያን ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለመሆን ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
በየጊዜውም ከዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ምን ያህል የተግባር፣ የጽንሰ-ሃሳብ እውቀት አላቸው የሚለውን ለመፈተሽ ይረዳል ነው ያሉት።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፤ የመውጫ ፈተናው የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባሻገር ምሩቃንን በአግባቡ በመለካት ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ተማሪዎች በተማሩባቸው የትምህርት መስኮች በአገሪቱ እድገት ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎች ለመውጫ ፈተናው አተገባበር ጠንካራ የሆነ የክትትል ስርአት መዘርጋት አለበት ብለዋል።
ውስጣዊ አደረጃጀታቸውን በማጠናከር በእያንዳንዱ የትምህርት ፕሮግራም ውስጥ ባሉ ትምህርቶች ላይ እውቀት፣ ክህሎትና አስተሳሰብ መለካት የሚችል ስርአት መዘርጋት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።
ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች የሚሰጠው የመውጫ ፈተና ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ተገልጿል።