51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዛሬው እለት ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዛሬው እለት ይጠናቀቃል
መጋቢት 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) 51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 10 የፍፃሜ ውድድሮች ተደርገውበት በዛሬው እለት ይጠናቀቃል።
51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከመጋቢት 19 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም እየተካሄደ ይገኛል።
በሻምፒዮናው ከዘጠኝ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ከክለቦችና ተቋማት የተውጣጡ አትሌቶች እየተካፈሉ ይገኛሉ።
የውድድሩ መርሃ ግብር ዛሬ የሚጠናቀቅ ሲሆን በ10 የፍፃሜ ውድድሮች ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግ ይሆናል።
በዛሬው እለትም በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉበት የ5 ሺህ ሜትር የወንዶች የፍፃሜ ውድድር ይደረጋል።
በውድድሩ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ አትሌት ሙክታር እንድሪስ እና አትሌት ጌትነት ዋለ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
በ5 ሺህ ሜትር የሴቶች የፍፃሜ ውድድር ደግሞ መልክናት ውዱ፣ መሰረት አበባየሁን ጨምሮ ሌሎችም አትሌቶች ይካፈላሉ።
የ1 ሺህ 500 ሜትር ወንድ እና ሴቶች ውድድሮችም በዛሬው መርሃ ግብር ይጠበቃሉ።
በሁለቱም ፆታዎች አራት በመቶ እና አራት በአራት መቶ የዱላ ቅብብል ፍፃሜ ውድድርም ይካሄዳል።
በወንዶች ከፍታ ዝላይ እንዲሁም በሴቶች የጦር ውርወራ የፍፃሜ ውድድርም እንዲሁ።