የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ትስስራቸውን ማጎልበት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ትስስራቸውን ማጎልበት አለባቸው
መጋቢት 23/2014/ኢዜአ/ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ቀጣናዊ ትስስራቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ተገለጸ።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለሰልጣን (ኢጋድ) ያዘጋጀው የ'ብሉ ኢኮኖሚ' ስትራቴጂ በአባል አገራት አስተባባሪ ሚኒስቴሮች ጸድቋል።
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኢጋድ አባል አገራት ውሃን መሰረት ያደረገ (በብሉ ኢኮኖሚ) ዘርፍ ዜጎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል እምቅ ሃብት አላቸው ብለዋል።
የቀጣናው የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና በዝናብ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለድርቅ፣ ምጣኔ ሃብት ቀውስ፣ የምግብ እጥረት፣ የሃብት ግጭቶችና አየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ተጠቂ አድርጎታል።
የውቅያኖስ፣ የሀይቅና የባህር ሀብቶችን እንዲሁም ወደቦችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ ብሉ ኢኮኖሚን ከችግሩ ለመውጣት አማራጭ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሳ ልማት፣ ትራንስፖርት፣ ቱሪዝምና ሌሎች ከውሃ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ምጣኔ ሃብቶችን አገራቱ በትብብር በመጠቀም የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት አለባቸው ብለዋል።
የምጣኔ ሃብት እድገታቸውንና የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በብሉ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከሆኑ አገሮች ልምድ መውሰድ እንደሚገባም የካናዳና ሌሎች አገሮችን ተሞክሮ ጠቅሰዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ፤ ዘርፉን ለመጠቀም ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን ተግባር በዝርዝር አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት አገር እንደመሆኗ የብሉ ኢኮኖሚ መዘጋጀትን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከአገራዊ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፖሊሲ እንዲሁም ሌሎች እስትራቴጂዎች ጋር በማጣጣም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአለም የምግብ ፕሮግራም የምስራቅ አፍርካ አስተባባሪ ዶክተር ቺሚምባ ዴቪድ፤ የአፍሪካን በተለይም የምስራቅ አፍሪካን ብሉ ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመጠቀም መንግስታት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የአሳ ልማትና አኳካልቸር አስተዳደርን ማጠናከርና በመንግስታት መካከል ትብብርን በማጠናከር የምግብ ዋስትናን በዘለቂነት ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
ድርጅታቸው ብሉ ኢኮኖሚ እስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል አገሮች የ'ብሉ ኢኮኖሚ' ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል።
ለቀጣይ አምስት አመታት በኢጋድ አባል አገሮች ተግባራዊ የሚደረገው የ"ብሉ ኢኮኖሚ" እስትራተጂ አካታችና ዘላቂ ብሉ ኢኮኖሚ በማልማት ለቀጣናው የኢኮኖሚ ሽግግር አስተዋጽኦ የማድረግ ራዕይ ሰንቋል።