የኢንስቲትዩቱን የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢንስቲትዩቱን የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና የጎላ ነው
አዳማ ፤ መጋቢት 23/2014 (ኢዜአ) የአርማወር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት በበሽታ አምጭ ባክቴሪያና ቫይረስ ላይ የሚያካሄዳቸው የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና የጎላ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታወቁ።
ኢንስቲትዩቱ በሚያከናውናቸው የምርምር ስራዎችን ወደ ተጠቃሚው አካላት በሚደርሱበትና የማህበረሰቡን የጤና ችግሮች ለመፍታት ከግልና የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት ከተውጣጡ ባለሙያዎች ጋር በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየመከረ ነው።
በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለምሰገድ አብዲሳ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበሽታ አምጭ ባክቴሪያዎችና ቫይረስ ላይ የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ ማህብረሰብ ለማድረስ የሚዲያ ባለሙያዎች ሚና የጎላ ነው።
ኢንስቲትዩቱ ለጤና ስርዓቱ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ በስጋ ደዌ፣መድኃኒት በተላመዱ ቲቢና ወባን ጨምሮ ሌሎች በሽታ አምጭ ትኩረት የሚሹ ቫይረስና ባክቴሪያ ላይ ምርምሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስና በክትባቱ ዙሪያ ምርምሮች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይነት በወረርሽኝ መልክ ሊነሱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል አቅም እየተገነባ ነው ብለዋል።
መድኃኒት የተላመዱ ቫይረስና ባክቴሪያ ዳግም በወረርሽኝ መልክ እንዳይነሱ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ኢንስቲትዩቱ በውድድር ከ70 በላይ የሚሆኑ የባዮ ሜዲካልና ክሊኒካል እንዲሁም የፋርማቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ተመራማሪዎችን በመቀበል በበሽታ አምጭ ባክቴሪያዎች ፣በቫይረስና በሌሎች ተዋህሲያን ላይ ምርምር እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በምርምሩ የማህበረሰብ ተሳትፎ እንዲካተትና ውጤቱም ወደ ማህበረሰቡ ደርሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ረገድ የሚዲያ አካላት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢንስቲቲዩቱ የአስተዳደርና ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ላምሮት አንዷለም ናቸው።
መድረኩ ጋዜጠኞች ማህበረሰቡ በምርምር ሥራዎች እንዲተባበርና እንዲያግዝ፣ውጤቱን ተቀብሎም እንዲጠቀም እንዲሁም የኢንስቲትዩቱን ተልዕኮና የዕለት ተዕለት ሥራ አውቀው እንዲያሳውቁ ያለመ ነው ብለዋል።
በተለይ እውቀትን ለማስረፅ በምርምር ውጤቶች ላይ በጋራ ለመስራት ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፣ በባዮ ሜዲካልና ክሊኒካል ዘርፎች የሚከናወኑ ሥራዎች የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ጥራት ከማጎልበት ጀምሮ ሂደቱን ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ የማህበረሰቡ የጤና ችግሮችን ለመፍታት በሚያከናውናቸው የምርምር ሥራዎች በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውቀዋል።
በተለይ በባዮ ሜዲካልና ፋርማሲቱካል ዘርፎች ላይ በትብብር የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን የልህቀት ማዕከል መገንባቱን አመልክተው፣ በፋርማሲቱካል ኢንዱስትሪ ልማት ላይ ለመስራት የምርምር ፓርክ ግንባታም እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።
የአርማወር ሀንሰን ምርምር ኢንስቲትዩት ከ52 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ከስዊድንና ከኖርዌይ ሕጻናት አደን ድርጅቶችና በበርገን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ያቋቋመው በጤና ላይ ምርምርና ጥናት የሚያደርግ መንግስታዊ ተቋም መሆኑን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።