በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአራት ማዕከላት በውድ ዋጋ የተገዙ ንብረቶች ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው ለብክነት ተዳርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአራት ማዕከላት በውድ ዋጋ የተገዙ ንብረቶች ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው ለብክነት ተዳርገዋል
መጋቢት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአራት ማዕከላት በውድ ዋጋ የተገዙ ንብረቶች ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው ለብክነት መዳረጋቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የንብረት አስተዳደር የኦዲት ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
ቋሚ ኮሚቴው 2012/13 በጀት ዓመት የንብረት አስተዳደር አፈጻጸምና ውጤታማነት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በአገልግሎቱ አራት ማዕከላት ላይ በተደረገ ኦዲት በርካታ ጉድለቶች ታይቷል።
ኦዲቱ ከ2010 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የሎጂስቲክስ፣ ንብረትና ፋሲሊቲ ዳይሬክቶሬት ዴስክ ላይ በምጣኔ ኃብታዊ፣ በቀልጣፋነትና ውጤታማነት በአራት ማዕከላት ላይ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በ2006 ዓ.ም ንብረቶችን የሚያስተዳድርበት ፖሊሲና መመሪያ ቢያወጣም በናሙና በታዩት በጎፋ ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት፣ በኮተቤ የተሸከርካሪ ጥገናና የትራንስፖርት አስተዳደር፣ በምዕራብና በደቡብ አዲስ አበባ ዲስትሪክቶች የዕቃ ግምጃ ቤቶች ላይ መመሪያው አልተተገበረም ብለዋል።
በአገልግሎቱ የኦዲት ቡድኑ በጎፋ የማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት ከያዙት ግዙፍ፣ ብዛት ያላቸውና ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ንብረቶችን ባገናዘበ መልኩ የሰው ኃይል በአግባቡ ባለመደራጀቱ የንብረት ብክነት አጋጥሟል ብለዋል።
በአራቱም የዕቃ ግምጃ ቤቶች ድንገተኛ ቆጠራ የማይካሄድ በመሆኑ በውድ ዋጋ ያላቸው ንብረቶች ለብክነትና ለስርቆት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በጎፋ ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት ከ7 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገዙ ብዛታቸው 8 ሺህ 601 የሆኑ ዕቃዎች ከ15 ዓመት በላይ በመጋዘን ቁጥር ሁለት ውስጥ ታሽጎ እንደሚገኝ በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል።
በተመሳሳይ የተሽከርካሪ ጥገናና ትራንስፖርት አስተዳደር በመጋዘን 13 ከ10 ዓመት በላይ አገልግሎት ሳይሰጡ 3 ሺህ 595 የተሽከርካሪ ዕቃዎች በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል።
በተቃራኒው 35 ሚሊዮን ብር በላይ ለተሽከርካሪ ኪራይ መከፈሉን ጠቁመው፤ በሥራ ላይ ያሉትም ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ጠቋሚ ጌጅ በትክክል እንደማይሰራ ገልጸዋል።
በደቡብና በምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክቶች በከፍተኛ ዋጋ የተገዙ ትላልቅ ንብረቶች እየተዘረፉ መሆኑን በኦዲት ግኝት ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።
ቋሚና አላቂ ንብረቶችን ከብልሽትና ከምዝበራ ለመከላከል በተሟላ ሁኔታ ቁጥጥርና ክትትል ባለመኖሩ ንብረት እየባከነ ይገኛል ሲሉም ጠቁመዋል።
በጎፋ ማዕከላዊ ዕቃ ግምጃ ቤት ከ5 ሺህ በላይ ዕቃዎች ለረዥም ጊዜ የተቀመጡና ከዚህም ውስጥ ከ651 ብቻ ሲታዩ ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን በኦዲት ተገኝቷል ብለዋል።
ከተቋሙ ሁለት ተሽከርካሪዎች አንድ V8 እና አንድ ሌላ ተሽከርካሪ መጥፋታቸውን በኦዲት ግኝቱ መታወቁንም ጠቅሰው፤ የንብረት አቀማመጥ፣ የቆይታ ጊዜና ለብልሽት የተጋለጠና ለመቆጣጠረ የሚያስቸግር አሰራር በተቋሙ ውስጥ መኖሩን ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው፤ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎርመር በብዙ ቦታዎች እየተበላሸ ኅብረተሰቡን እያስቸገረና በመንግሥትም ላይ ቅሬታ እያስነሳ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጎን ለጎንም ተቋሙ ንብረት የሚዘረፍበት፣ የሚባክንበት፣ ሰፋ ያለ ሌብነት ያለበት መሆኑን የቋሚ ኮሚቴ አባላት አንስተው፤ አገልግሎቱ የተገኘውን የኦዲት ሪፖርት መሰረት ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መሥራት አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው፤ በፌደራል ኦዲተር መሥሪያ ቤት በተገኙ ግኝቶች መሰረት የተለያዩ መፍትሔዎች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡ በዘመናዊ መንገድ በዲጂታል ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸው፤ ንብረት እንዳይባክን የአራት ሰፋፊ መጋዘኖች ግንባታ መጠናቀቁንና የደህንነት ካሜራ እንደተገጠመላቸው ጠቁመዋል።
ሌብነትን ከመከላከል አንጻርም በ2013 ዓ.ም ብቻ በብልሹ አሰራር ላይ የተሳተፉ ከ900 በላይ ሰራተኞች በተለያየ ደረጃ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።
የተበላሹ 352 ተሽከርካሪዎች ጥገና ተደርጎላቸው ሥራ ላይ መሆናቸውንና 400 ተሽከርካሪ ግዥ ተፈጽሞ የተሸከርካሪ ኪራይ ማስቀረቱን ተናግረዋል።
የጠፉትን ሁለት ተሽከርካሪዎች በተመለከተ አንዱ V8 በሌላ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት በሥራ ላይ መሆኑን እንዲመለስ ንግግር መጀመሩን ገልጸዋል። ያም ሆኖ አንዱ ተሽከርካሪ ግን ቤንሻንጉል ክልል ውስጥ ጠፍቶ አለመገኘቱን ጠቁመዋል።
የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክሪስቲያን ታደለ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ ህዝቡ የሚጠብቀውን የተቀላጠፈ የንብረት አጠቃቀምና አያያዝ በብርቱ ሊሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት የቆይታ ዘመኑንና ልምዱን ታሳቢ ያደረገ ቀልጣፋ አገልግሎት ለህዝቡ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል። አሁን ላይ ያለውን የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ችግር ሊፈታም እንደሚገባም አሳስቧል።
ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶባቸው የተገዙ ንብረቶች ያለአገልግሎት እስከ 20 ዓመታት መቀመጣቸውን ጠቅሰው፤ በተቃራኒው ደግሞ ኅብረተሰቡ በኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ችግር ውስጥ መገኘቱ ሊታሰብበት እንደሚገባ አመላክተዋል።
ከዚህም ይባስ ብሎ እስከ ንጉሱ ዘመን ድረስ ያለአገልግሎት የተቀመጡ ንብረቶች በመኖራቸው በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተላቸው ቁርጠኛ አቋም በመውሰድ ሊስተካከል እንደሚገባም አሳስቧል።
አሁን አገሪቷ በምትፈልገው ልክ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሕዝቡን ፍላጎት ለሟሟላት አገልግሎቱ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ቋሚ ኮሚቴውም ያለውን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያለውን የንብረት አያያዝ ችግር እንዲፈታ የሚከተሉትን አቅጣጫዎች አስቀምጧል ብለዋል።
አገልግሎቱ እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እርምጃዎችን፣ የተፈጸሙና በሂደት ላይ ያሉ ያልተፈቱ ችግሮችን ለይቶ ሪፖርት ሊያቀርብ ይገባል ሲል አሳስቧል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በሕዝብ ኃብትና ንብረት ላይ መሰል ብክነት ያደረሱ የአገልግሎቱ የሥራ ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን በየሥልጣን እርከኑ ያሉ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ወስዶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያሳውቅ አሳስቧል።
አገልግሎቱ ከመሰል የአስተዳደርና ዝርክርክነት የሚያወጣበትን የመፍትሔ አማራጭ ደግሞ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ሚኒስቴሩ ለቋሚ ኮሚቴው ማሳወቅ አለበትም ብለዋል።
የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ በተቋሙ ያሉ አሰራሮችን አስተዳደሮች ላይ ለሙስናና ብልሹ አሰራር አጋላጭ ጉዳዮች ካሉ አጥንቶ ሪፖርቱን ከውሳኔ መነሻ ሐሳብ ጋር በሁለት ወራት ውስጥ ማቅረብ አለበት ብለዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ጉዳዮች ካሉ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ የደረሰበትን ውጤት በሁለት ወራት ውስጥ እንዲያሳውቅና ክስም እንዲመሰረት አቅጣጫ ተቀምጧል ሲሉም ጠቁመዋል።
የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴር በተቋሙ ላይ የተገኙ ጉዳዮችን በ100 ቀናት እቅዱ አካቶ መያዙን የማረጋገጥና የኦዲት ግኝት ማስተካከያ ማድረጋቸውን ተገቢውን ክትትል እንዲያደርግም ብለዋል።