ረቂቅ አዋጁ በትራንስፖርት መሰረተ ልማት ዘርፍ የግል ባለኃብቱ የሚሳተፍበትን መንገድ ማካተት እንዳለበት ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ አዋጁ በትራንስፖርት መሰረተ ልማት ዘርፍ የግል ባለኃብቱ የሚሳተፍበትን መንገድ ማካተት እንዳለበት ተገለጸ
መጋቢት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመንገድ ትራንስፖርት ረቂቅ አዋጅ የትራንስፖርት ዘርፍ ልማት ላይ የግል ባለሃብቱ በትብብር የሚሳተፍበትን መንገድ ማካተት እንዳለበት ተገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከትራንስፖርተሮች ማኅበርና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
ላለፉት 17 ዓመታት እያገለገለ ያለው የትራንስፖርት አዋጅ ቁጥር 468/1997 አገሪቱ ካለችበት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት አንጻር ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ በሚል ስያሜ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
ከረቂቅ አዋጁ ዓላማዎች መካከል አስተማማኝ፣ የተቀናጀ፣ ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነት እንዲሁም የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ደህንነትን ማረጋገጥ ይገኙበታል።
ቀጣናዊ የትራንስፖርት ትስስር በማጠናከር፣ ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ የሎጂስቲክ አፈጻጸም፣ ውጤታማነትን ማጎልበትም የአዋጁ ዓላማዎች ናቸው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ረቂቅ አዋጁ በዘርፉ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም በረቂቅ አዋጁ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተሰጡ አንዳንድ ሥልጣንና ተግባራት ሚኒስቴሩን ከማስተባበር ወደ ፈጻሚነት የተሰማራ ያስመስለዋል ብለዋል።
ለአብነት ሚኒስቴሩ የባለሞተር ተሽከርካሪዎች ማቆሚያን፣ የህዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያዎችን፣ የአውቶቡስ ዴፖን፣ የጭነት ተርሚናሎችን ደረጃዎች ከመወሰንና አተገባበር ከመከታተል ባለፈ እንደ አስፈላጊነቱም እነዚህን የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች ያስፋፋል፤ ያስተዳድራል የሚለውን አንስተዋል።
ተወያዮቹ ሚኒስቴሩ የማስተባበር ሚናውን እንዲወጣና መሰል የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በባለሃብቱ እንዲሁም በመንግስትና ግል አጋርነት ሊከናወኑ እንደሚገባ በረቂቅ አዋጁ መመላከት እንደሚገባው ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ከመሰረተ ልማት ግንባታ ይልቅ ባለሃብቱ በመሰል ሥራዎች ለመሰማራት ማሟላት የሚገባውን መስፈርቶች ማዘጋጀትና መሰል ሥራዎችን እንደሚሰራ በረቂቁ ቢመላከት የሚል ሐሳብም አክለዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመን አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የሌሎች አገሮችን ልምዶች በሚገባ መቀመርና በአዋጁ ማካተት ይገባልም ብለዋል።
የህዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ በነጻ ገበያው የሚመራበት አግባብ መኖር እንደሚገባውም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።
በረቂቁ የተቀመጡ ቴክኒካል ቃላት ፍቺና አጠቃቀም በሚገባ ሊታይ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።
ተወያዮቹ በህጎች ውስጥም ሆነ በአተገባበራቸው ላይ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ሊካተት እንደሚገባም አንስተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ላለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ አካላት ሲወያዩበት ቆይቷል።
የሚኒስቴሩን የአሥር ዓመት እቅድ ለመተግበር ከ3 ትሪሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በመንግስት አቅምና በጀት ይፈጸማል ብለን አናምንም ብለዋል።
ስለሆነም የተለያዩ መሰረተ ልማቶች፣ ዴፖዎችና መናኸሪያዎችን እንደ መንግሥት ለብቻ ማልማት አንፈልግም የግል ባለኃብቱን ተሳትፎ እንፈልጋለን ነው ያሉት።
ሆኖም የግል ዘርፉ የተሽከርካሪዎችን የምልልስ ቁጥርና የሚያገኘውን የደንበኛ መጠን አስልቶ ወደ ልማቱ የሚገባ በመሆኑ በጋራ በቅንጅት የሚሰራበት አግባብ በሕግ ማዕቀፍ ተቀምጦ የግል ባለኃብቱ እንዲሰማራ ፍላጎት እንዳለ ተናግረዋል።
ከቃላት አጠቃቀም ጋር ያሉ ውስንነቶች እንደሚታረሙና በውይይቱ የተነሱ ሐሳብና አስተያየቶች በግብዓትነት የሚካተት መሆኑንም አስረድተዋል።
የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው፤ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የአዋጁ መሻሻል ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
ረቂቅ አዋጁ ፀድቆ ወደትግበራ እንዲገባ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሊካተቱ የሚገባቸው ሐሳብና አስተያየቶች እስከ መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ለቋሚ ኮሚቴው ማቅረብ እንደሚቻል ተናግረዋል።