የአዲስ አበባ ከተማ ስተዳደር ንግድ ቢሮ የበዓል ገቢያውን የሚያረጋጋ የቅድመ ዝግጅት ስራ ማድረጉን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ ስተዳደር ንግድ ቢሮ የበዓል ገቢያውን የሚያረጋጋ የቅድመ ዝግጅት ስራ ማድረጉን አስታወቀ
አዲስ አበባ ነሀሴ30/2010 የአዲስ አበባ ከተማ ስተዳደር ንግድ ቢሮ የበዓል ገበያውን የሚያረጋጋት የቅድመ ዝግጅት ስራ ማድረጉን አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በፍጆታ እቃዎች ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል። በተለይም በመጪው አዲስ ዓመት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮዽያውያንና ትውልደ ኢትዮዽያውያን ወደ አገር እንደሚገቡ በማሰብ በፍጆታ ምርቶች ላይ ከወትሮው በተለየ የተሻለ አቅርቦት እንደሚኖር ኃላፊው ገልፀዋል። ለአብነትም ከዚህ በፊት በየወሩ ለከተማዋ ይቀርብ የነበረው 120ሺ ኩንታል ስኳር ኮታ ላይ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ተጨማሪ 5ሺህ ኩንታል ስኳር እንዲቀርብ መደረጉን ተናግረዋል። ሸማቾችን ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር በማስተሳሰር ከ26ሺህ ኩንታል በላይ የፍጆታ ምርቶች በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት መዘጋጀቱንና ከሸማቾች ማህበራት ጋር የማስተሳሰር ተግባራትም መከናወኑ ተገልጿል። ለበዓሉ ከወትሮው በተለየ ህብረተሰቡ በብዛት የሚፈልጋቸው እንስሳትና የእንስሳት ተዋጾዎችንም ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ መደረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ በበኩላቸው ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ሽንኩርት፣ እንቁላል፣ ዶሮና ሌሎች እንስሳት ከአዲስ አበባ አጎራባች አካባቢዎች በኅብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ወደ ከተማዋ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። እስካሁን ባለው ሂደትም ከ300 ሺህ በላይ እንቁላልና 2ሺህ300 ኩንታል ሽንኩርት ወደ ከተማዋ መግባቱንና 25ሺህ ዶሮዎች እንዲሁም የቁም እንስሳት እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። የምርት ስርጭቱ በትክክል እየተካሄደ መሆኑን የሚያረጋግጥና አላግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን እየተከታተለ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ ግብረ ኃይል በ116ቱም ወረዳዎቸ መዘጋጀቱ ተገልጿል።