ቀጥታ፡

ያለፉት አራት ዓመታት የመንግስት ውሳኔዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለነጻ ተቋማት ማቆጥቆጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል

መጋቢት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) ያለፉት አራት ዓመታት የመንግስት ውሳኔዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለነጻ ተቋማት ማቆጥቆጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን ለመምራት በሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሓላ የፈጸሙበት ዕለት ነው።

በዕለቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ የቀረ ታሪካዊ እንደነበር ይጠቀሳል።

በንግግራቸው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሊጫወቱ የሚችሉት ሚና አንዱ እንደነበር ይታወቃል።

ከታሪካዊዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጀምሮ በኢትዮጵያ ለውጡ እውን ከሆነ ወዲህ ባለፉት አራት ዓመታት ምን ውጤቶች ተመዘገቡ ሲል ኢዜአ ከብልጽግና ፓርቲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እና ከኢዜማ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ኢትዮጵያ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ  ወደ ስልጣን እንደመጡ ዶክተር ቢቂላ ያስታውሳሉ።

በመስቀለኛ መንገድ ላይ ሆና በርካታ ችግሮች ተጋርጠውባት የነበረችውን አገር ተረክበው በታታሪነት በመምራት ህልውናዋን በማስቀጠል መንግስት የነበረውን ሚና አንስተዋል።

በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ባለፉት አራት አመታት ለትውልድ መሰረት የሚሆን ስራ ተከናውኖ የላቀ ውጤት የተገኘበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የመንግስት ውሳኔዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለነጻ ተቋማት ማቆጥቆጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ዶክተር ቢቂላ አብራርተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለምንም ጫና ሀሳባቸውን ሸጠው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ አዲስ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

ፓርቲዎች በጋራ የሚመሩበት ስርዓት በማዘጋጀት እንዲሁም የህግ ማእቀፍ በማስተካከል መልካም ውጤቶች መገኘታቸውንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን በመገንባት ሂደትም ያለፉት አራት ዓመታት ስኬት የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ ኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፤ ባለፉት አራት አመታት የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች ትርጉም ያላቸውና አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በውጭ ሆነው ትግል ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎች ወደ አገራቸው ገብተው የሃሳብ ትግል የማድረግ አጋጣሚ ያገኙበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የግል መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ስራቸውን በነጻነት እንዲያከናወኑ መደረጉም ሌላው ምልካም ውሳኔ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ምርጫ ቦርድን የመሳሰሉ ነጻና ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመመስረትና በማጠናከርም መልካም ጅማሮ ታይቷል ብለዋል።

በቀጣይም መንግስት ችግሮችን ሰላማዊና አሳታፊ በሆነ መገድ ለመፍታት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት የጋራ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም