የረመዳን ጾም ነገ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የረመዳን ጾም ነገ ይጀመራል
መጋቢት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የረመዳን ጾም ነገ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
ጾሙ ነገ የሚጀመረው የረመዳን ወር ጨረቃ ዛሬ በተሟላ መልኩ በመታየቷ እንደሆነ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ የረመዳን ወር ጾምን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ ታላቁን የረመዳን ወር በጎ ተግባር በመፈጸም ማሳለፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የረመዳን ወር የመረዳዳት፣ የመተጋገዝና የመከባበሪያ ወር በመሆኑ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ፈጣሪ የሚወደውን በጎ ተግባራትን በማከናወን ጾሙን ማሳለፍ እንዳለበትም አሳስበዋል።
ረመዳን በሂጅራ አቆጣጠር ዘጠነኛው ወር እና በሙስሊሞች ዘንድ የጾምና ጸሎት ወር ነው።
ረመዳን ከአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት ዉስጥ አንዱ ሲሆን፤ ጾሙ ለሃያ ዘጠኝ ወይም ሰላሳ ቀናት ይቆያል።