ቀጥታ፡

የመንግስት የኦንላይን አገልግሎት ክፍያዎች በዲጂታል አማራጭ እንዲፈፀሙ ሊደረግ ነው

መጋቢት 23/2014/ኢዜአ/ የመንግስት የኦንላይን አገልግሎት ክፍያዎች በዲጂታል አማራጭ እንዲፈፀሙ ሊደረግ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች እና ማስተርካርድ የክፍያ አገልግሎቱን ለማዘመን ተስማምተዋል።

አዲሱ አሰራር የማስተርካርድ የክፍያ አማራጭን ከኤሌክትሮኒክ ሰርቪስ አገልግሎት ፖርታል ጋር በማቀናጀት ዜጎች የመንግስት አገልግሎት ክፍያዎችን በኦንላይን እንዲፈጽሙ ያስችላል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ፤ አሰራሩ የኢትዮጵያን የክፍያ ስርዓት በማዘመንና አካታች የፋይናንስ አገልግሎት በማዘመን የመንግስትን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል።

"የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025" የኢትዮጵያ ዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ እቅድን ለማሳካት የላቀ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

"የእኛ ጥረት ኢትዮጵያን ከጥሬ ገንዘብ ህትመትና ስርጭት ጥገኝነት በማላቀቅ ዓለም አቀፍና ዘመናዊ የፋይናንስ ስርአት እውን ማድረግ ነው" ብለዋል፡፡

የማስተር ካርድ የምሥራቅ አፍሪካ ሥራ አስኪያጅ ሸርያር አሊ፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ ፈጣንና ደኅንነቱ የተጠበቀ ዲጂታል የክፍያ አማራጭ በመገንባት ሂደት በትብብር እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

እውን የሚሆነው አሰራር ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት የላቀ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር የማስተር ካርድ ዲጂታል የክፍያ ስርአት በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅት ተግባራዊ ተደርጓል።

ድርጅቱን ወክለው የተገኙት አቶ ፋሲካው ሞላ፤ የማስተርካርድ ድጅታል ክፍያ ስርዓት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አለም አቀፍ ይዘት ያለው የማስተር ካርድ የክፍያ ስርዓት ከዘመናዊነቱ ባሻገር ሰዎች ያለእንግልት ባሉበት ቦታ ሆነው ክፍያ መፈፀም ያስችላቸዋል።

በሁሉም የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በቀጣይ ተግባራዊ የማድረግ እቅድም ተይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም