ቀጥታ፡

በሳውዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ሺህ 800 ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል

መጋቢት 23/2014/ኢዜአ/ በሳውዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ ሁለት ሺህ 800 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት መመለስ መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ  ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ብሔራዊ አስፈፃሚ ኮሚቴ በማዋቀር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱ ይታወሳል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ከ2 ቀናት በፊት ወደ ሃገር ቤት የመመለስ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

በዛሬው እለት በጂዳ እና አካባቢው ባሉ እስር ቤቶች እና ማቆያ ማዕከላት ውስጥ የነበሩ 1 ሺህ 173 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሃገር ቤት ተመልሰዋል።

ተመላሾቹ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሀላፊዎች ተቀብለዋቸዋል።

ከትላንት በስቲያ በተጀመረው በሳኡዲ አረቢያ እስር ቤቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን የመመለስ ስራ በአንድ ቀን  ከሪያድ 936 ኢትዮጵያዊን ማምጣት ተችሏል።

በዛሬው ዕለት በተደረጉ አራት በረራዎች 1 ሺህ 173 ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ የተቻለ  መሆኑን አብራርተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዳሉት ፤ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ  ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በሳምንት ዘጠኝ በረራ በማካሄድ የመመለስ ስራ ተጀምሯል ያሉት አምባሳደሯ፣ በአንድ በረራ 480 ዜጎች እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል።

በዚህ መሰረት እስካሁን ወደ  2ሺህ 800 የሚሆኑ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት መመለስ መቻላቸውን ተናግረዋል።

በእቅዱ መሰረት በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ  ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የኢሚግሬሽን ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ግንበቶ በበኩላቸው ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ያሉት ዜጎች ከሀገር ደህንነት አንፃር ትክክለኛ ማጣራት ስራ ተሰርቶ  ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፤ ወደ ሀገራቸው የገቡ ዜጎችን ወደ የመጡበት ክልል የመመለሱ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የተመለሱ ዜጎች ስልጠና በመስጠት መልሶ የማቋቋም ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከኢኮኖሚ ሟቋቋም ባሻገር የስነ-ልቦና ድጋፍ እየተደረገላቸው ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ እንደሚገኙ እና በቀጣይ በአካባቢያቸው የሚደረግላቸውን የስራ እድል ፈጠራ ታች ድረስ ተወርዶ የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመመለሱ ስራ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም