ቀጥታ፡

እስራኤል ለትንሳኤ በዓል ወደ ሃገሯ በሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ላይ ጥላ የነበረውን እገዳ ማንሳቷ ተገለጸ

መጋቢት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) እስራኤል ለትንሳኤ በዓል ወደ ሃገሯ በሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ላይ ጥላ የነበረውን የጉዞ እገዳ ማንሳቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የእስራኤል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ለሚመጡ ጎብኚዎች የቡድን ቪዛ በጣለው እገዳ በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገዳም አባቶችና የተለያዩ አካላት በውሳኔው ላይ አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጿል።

በእስራኤል የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከእስራኤል መንግስት ተቋማት ሃላፊዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ውሳኔው ከኢትዮጵያና እስራኤል የሁለትዮሽ ወዳጅነት አንጻር ተገቢ አለመሆኑ ሲገልጽ መቆየቱ ተነግሯል።

ኤምባሲው ከእስራኤል የፓርላማ አባልና የቀድሞው የእስራኤል የአገር ውስጥ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርካን ጋር በመሆን ከእስራኤል የሕዝብና ኢሚግሬሽን ባለስልጣን ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያኑ ላይ ተጥሎ የነበረው የጉዞ ገደብ እንደተነሳ በኃላፊዎቹ መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።

በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ ውሳኔው እንዲቀየር ላደረጉ አካላት ምስጋና በማቅረብ ውሳኔው በእየሩሳሌም የሚገኙ ቅዱሳን መካናትን ለመሳለምና ጸሎት ለማድረግ ለሚመጡ ሁሉ መልካም ዜና ነው ብለዋል።

የእስራኤል የፓርላማ አባልና የእስራኤል የቀድሞ የአገር ውስጥ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርካን በበኩላቸው “የእስራኤል አምላክ ፈቃድ ሆኖ ይህ መልካም ዜና ለኢትዮጵያዊያን በመድረሱ ደስታዬ ከፍ ያለ ነው ብለዋል”።

በእየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንባቆም እገዳው ተነስቶ የትንሳኤ በዓልን ለማክበር ከሚመጡት ኢትዮጵያዊያን ጋር መገናኘት እንደሚያስደስትና በዓሉን በእየሩሳሌም እንዲያከብሩ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም