ሀገራዊ ጫናን ለመቋቋም--- - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ጫናን ለመቋቋም---
በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)
ኢትዮጵያ ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ሀገራት የኩራት ምንጭ የሆነ የነጻነት ታሪክ ባለቤት ነች፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ምዕራባውያኑ ፍላጎታቸውን በግድ እና በሀይል ለመጫን የማዋከብ ስራ ላይ ቢጠመዱም፤ የነጻነት ቀንዲልነቷ ህልውናዋ በምዕራባውያን መልካም ፈቃድ ላይ እንዳይመሰረት በብዙ ረድቷታል፡፡ ይህ አይነት ፍላጎት ያላቸው ሀገራትና መንግስታት ፍላጎታቸውን እንዲፈጽሙ እንደማትፈቅድ ህዝብም ሆነ መንግስት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የአሜሪካም ሆነ የአንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ፍላጎት አንድም በኢትዮጵያ ላይ ለፍላጎታቸው የሚያድር የይስሙላ መንግስት ማስቀመጥ፤ ይህን የማይቀበል እና ሉዓላዊነትን አላስደፍርም የሚል መንግስትን ደግሞ በፖለቲካዊ ሴራ እና በኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ በማሽመድመድ ከስልጣን ለማስወገድ የሴራ ስራ መስራትን እንደ ስልት መጠቀም ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውም ይኸው ነው፡፡ የተለያዩ ማዕቀቦችን እንጥላለን የሚሉ ዛቻ እና ማስፈራሪያዎችን በመሰንዘር እና በማርቀቅ ጭምር መላ ህዝቡን ለችግር የሚያጋልጡ ውሳኔዎችን ለማስወሰን ዳርዳር እያሉ ያሉትም ከዚህ መነሻ ነው፡፡
የእነዚህ ሀገራት ቀደምት ሀገር የማፍረስ ተሞክሮ ሲቃኝ ከፊት የሚገኙት አፍጋኒስታን፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ዩክሬን እና መሰል ሀገራት ናቸው፡፡ ከምንም በላይ የሚገርመው እና በቅርቡም የታየው የእነዚህ ሀገራት እና ድርጅቶች አዲስ ባህሪ ደግሞ በርካታ ሀገራትን እና ህዝቦችን ለቀውስ ካጋለጡ እና ሀገራትን ካፈረሱ በኋላ “እኛ የለንበትም፣ ዜጎች ራሳቸውን ሊከላከሉ ይገባ ነበር፣ እኛ ሀገሪቱን ለመከላከል ወደ ሀገራቱ አልገባንም” የሚሉ ሀላፊነት የጎደለው መግለጫዎችን ሲያወጡ ማየት ነው። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን በራሷ የመፍታት አቅሙም ጥበቡም እንዳላት በተለያዩ ሀገራት መንግስታት፣ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ድርጅቶች እና ተቋማት ምስክርነት ሲሰጥ ቢቆይም ተረኛዋ መፍረስ ያለባት ሀገር መሆኗን ወስነው እየሰሩ መሆኑን በሚያስታውቅ መልኩ ያልተገባ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡
የአሜሪካ ሴናተሮች እና የኮንግረስ አባላት ‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ የተሰኙት ረቂቅ ህጎችን በማዘጋጀት ህግ ሆነው እንዲጸድቁ አቅርበዋል፡፡ እነዚህ ረቂቅ ህጎች የሚጸድቁ ከሆነ ኢትዮጵያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥገኛ ከማድረግ ባለፈ አሜሪካም ሆነች አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ማሳረፍ የሚፈልጉትን ጫና በነጻነት እንዲጥሉ መፍቀድ ማለት ነው፡፡ የረቂቅ ህጎቹ ሽፋን “አሜሪካ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአትን ለመገንባት፣ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣትና የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የምታደርገውን የዲፕሎማሲ፣ የልማትና ህጋዊ ድጋፍ ይበልጥ የማሳደግ አላማ ያለው ነው” ሲል በህጉ መግቢያ ላይ ይገልጻል። የህጉ መግቢያ ይህን ቢልም ይዘቱን በጥልቀት የፈተሹ ባለሙያዎች ግን የአንድን ሀገር አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያሽመደምዱ፤ መላ ህዝቡንም ለከፋ ችግር የሚዳርጉ ህጎች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ህግጋቱ ኢትዮጵያ እንደሀገር እንዳትቀጥል የሚያደርጉ አሳሪ ህጎች መሆናቸውን ተከትሎ እንዳይጸድቁ ከሚደረገው ርብርብ በተጨማሪ ጫናን መቋቋም የሚያስችል ሀገራዊ አቅም ሊገነባ እንደሚገባ ምሁራን ምክረ-ሃሳባቸውን እየሰነዘሩም ይገኛሉ፡፡
በአሜሪካ ህግ አወጣጥ ስርዓት መሰረት አሁን ህጉን የማስተዋወቅ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጹት የህግ ባለሙያዎች የተዘጋጀው ህግ አምስት ደረጃዎችን አልፎ በፕሬዝዳንቱ ከተፈርመ በኋላ ህግ እንዲሆን እንደሚጠበቅም ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዬን በራሴ የመፍታት አቅሙም፣ ስልቱም፣ ጥበቡም፣ ልምዱም አለኝ እና የእናንተን ጣልቃ ገብነት አልሻም፡፡ ድጋፋችሁንም ስፈልግ እኔው ራሴ ልጠይቃችሁ የሚል ምላሽ በተደጋጋሚ ብትሰጥም እነዚህ ሀገራት፣ መንግስታት እና ድርጅቶች ቀድሞውንም እኛ ያልገባንበት የሰላም ማስከበርም ሆነ የእርቅ ሂደት ትክክል አይደለም የሚል አይን ያወጣ አካሄድን የሚከተሉ በመሆናቸው ከሚዛናዊነት ያፈነገጡ እና የራስ ፍላጎትን ብቻ ታሳቢ ያደረጉ ትችቶችን፣ ወቀሳዎችን፣ የፈጠራ ክሶችን ጨምሮ የተለያዩ ማዕቀቦችን በሀገር ላይ ለመጣል እንቅስቃሴ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
በአሜሪካ የሚገኘው ጌትፋክት የተሰኘው የሲቪክ ተቋም በድረ-ገጹ ላይ እንዳስነበበው በተለይ ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ህግ ለኢትዮጵያ አደገኛ የሆነበትን ምክንያት ሲያስቀምጥ ህጉ የተረቀቀው በኢትዮጵያ ስላለው ግጭት የተዛቡ ዘገባዎችን መሰረት በማድረግ እንደሆነ ገልጿል። ኢትዮጵያውያን ላለፉት 30 ዓመታት የሕወሓት የጭካኔ ሰለባ ሆነው በተጽዕኖ እስከ ዛሬ ድረስ ቢቆዩም፤ ህጉ የሕወሓት ታጣቂዎችን ሳይሆን የኢትዮጵያን መንግስት ተጠያቂ እንደሚያደርግ አመልክቷል። የህጉ ረቂቅ ኢትዮጵያ ዜጎችን ከሕወሓት ሽብርተኝነት እንዳትከላከል እንደሚገድብና ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ፣ ሉዓላዊነትና ደህንነት አደጋ ላይ እንደሚጥል አስታውቋል።
በተሳሳተ መረጃ እና ዓላማ ላይ የተመሰረቱት እነዚህ ረቂቅ ህጎች እንዳይጸድቅቁ እርምጃ ካልተወሰደ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉትን ጉዳቶች ያመጣል ሲል የገለጸው ይኸው ተቋም፤ እነሱም በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣልን፤ ኢትዮጵያን እንድትገለል ማድረግን፤ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የቪዛ ቅነሳና ስረዛ ማድረግን፤ ሁሉንም የአሜሪካ ኢንቨስትመንቶችና የገንዘብ ልውውጦች ማገድን፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የጸጥታና የልማት ድጋፍ መገደብን፤ አሜሪካ ተሰሚነቷንና ድምጽ የመስጠት መብቷን ተጠቅማ ኢትዮጵያ ብድርና የብድር ማራዘሚያ ክልከላ እንዲደረግ ግፊት ማድረግን፤ አሜሪካ ህጉን ተጠቅማ ኢትዮጵያ ማንኛውንም የውትድርና ድጋፍ እንዲሁም ግዢ እንዳታገኝ ጫና ማሳደርን፤ አሜሪካ የዓለም አገራትና የዓለም የፋይናንስ ተቋማትን በማስተባበር ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን እርዳታ መገደብን እንደሚካትት ድርጅቱ አስነብቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም ረቂቅ ህጎቹ ቢጸድቁ የሚያስከትሉትን ሀገራዊ ጫና ግምት ውስጥ በማስገባት እንዳይፀድቁ ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል ሲል ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈን በርካታ ጥረቶችን እያደረገች ስለመሆኑ መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም ይህንን ጥረት ወደ ጎን የጣሉ ‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ የተሰኙት ረቂቅ ህጎች መዘጋጀታቸው የሀገራቱን ግንኙነት በመሰረታዊነት የሚጎዳ ስለመሆኑም መንግስት እና የዘርፉ ምሁራን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ አሜሪካ እና አንዳንድ ምዕራባውያን “እኛ ያልወጠወጥነው … “ የሚለውን ብሂል በሚያስታውስ መልኩ አይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ለዚህም ያልናችሁን ካልፈጸማችሁ ወዮላችሁ እያሉ ማስፈራራት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ አገራት እንዲህ አይነት የውጭ ጣልቃ ገብነት ሲገጥማቸው በራሳቸው ስራ ፈጠራ ጥበብ መሻገር እንደቻሉ ጃፓን ለአብነት የምትጠቀስ ሀገር ነች። ኢትዮጵያም አሁን ላይ የገጠማትን ውስጣዊና ውጫዊ ተጽዕኖዎችን ተቋቁማ መሻገር ከፈለገች በስራ ፈጠራ ጥበብ ላይ በማተኮር በየትኛውም ስራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ጊዜን፣ ሙያንና ጉልበትን በመጠቀም በትጋት እንዲሰሩ መደረግ ብቸኛ አማራጭ ስለመሆኑ በስራ ፈጠራ ዙሪያ ሰፊ ልምድ ያካበቱት ዶክተር ወሮታው በዛብህ ይመክራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በውስጥ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለምፍታት ከወሰደቻቸው እርምጃዎች መካከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜው ሳይደርስ ማንሳት፣ ከፍተኛ ፖለቲካ አመራሮችን ከእስር መልቀቅ፣ ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተናጠል የተኩስ ማቆም መወሰን፣ ለትግራይ ህዝብ የሰብዓዊ ድጋፎች እንዲገቡ የአየር እና የየብስ ትራንስፖርት መፍቀድ፣ የሽብር ቡድኑ ህልውና የተመሰረተው በተራዘመ ጦርነት ላይ ብቻ በመሆኑ ለትግራይ ህዝብ በፌዴራል መንግስቱ እየቀረቡ ያሉ የሰብዓዊ ድጋፎች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ መንገድ መዝጋት፣ አዋሳኝ ኮሪደሮች አካባቢ ጦርነት መቀስቀስ እና ማስፋፋት የመሳሰሉ የአደናቃፊነት ሚናውን እንዲያቆም ለሽብር ቡድኑ ዕድል መስጠት፣ የዓለም ማህበረሰብም እውነታውን እንዲያውቅ ማድረግ እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኮንግረስ አባላት እና ሴኔት አባላት ተዘጋጅተው የቀረቡት ‘ኤች አር 6600’ እና ‘ኤስ.3199’ የተሰኙ ረቂቅ ህጎች ይዘት ጸድቀው በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ቢደረጉ እንደሀገር የሚያስከትለው ችግር ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ አይመጣምን ትተሸ ይመጣልን አስቢ የሚለውን ብሂል በማስታወስ መንግስት እና መላ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ የግድ መሆኑንም እንዲሁ፡፡ እንደ ዶክተር ወሮታው በዛብህ ሙያዊ ማብራሪያ ከሆነ ኢትዮጵያ ያላትን መሬት፣ የሰው ሀብት፣ ካፒታል፣ የስራ ፈጠራ ሃሳብና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን አሟጣ በመጠቀም ጫናዎችን መቋቋም የሚያስችላትን አቅም መፍጠር ትችላለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከገጠማት አገራዊ ችግርና ዓለም አቀፋዊ ጫና አንጻር ገቢ ምርቶችን የሚተኩና ያልተሟሉትን ምርቶች የሚያመርቱ የስራ ፈጣሪዎችን ቁጥር የማብዛት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡
“በአሜሪካ የሚገኙ ዜጎች የህጎቹን አስከፊነት ሲገልጹትም ጥረን ግረን የምናገኘውን ገንዘብ እንኳን ወደ አገራችን እንዳንልክ ቁጥጥር እንደሚያስደርጉ የዚህ ረቂቅ አቀንቃኞች እየነገሩን ነው። ሰው ለምን ስለሀገሩ መፃኢ ተስፋ ከራሱ ይልቅ በሌላው እንደሚተማመን አላውቅም። ነፃነት የሚገኘው ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሳይሆን ከራስህ ነው” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ለጊዜው በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ልዩ ልዩ ማህበራት በተወካዮቻቸው በኩል ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ረቂቅ ህጉን ባረቀቁት እና በኮሚቴው አባላት ሴናተሮች ላይ ባደረጉት ግፊት የተወሰኑ ሴናተሮች ረቂቅ ህጉን በደንብ ማየት እንደሚገባቸውና ጊዜ እንደሚፈልጉ በመግለጻቸው ምክንያት ኮሚቴው በህጉ ላይ ሊያደርግ የነበረው ውይይት በአንድ ሳምንት ቢራዝምም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም መንግስት ህጎቹ ህግ ሆነው እንዳይጸድቁ አስፈላጊውን ርብርብ ማድረግ እና አሉ የተባሉ ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን በሙሉ መጠቀም እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ህግጋት ህግ ሆነው እንዳይጸድቁ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት አመራሮች በቅርቡ ከአሜሪካ ሴኔት የዴሞክራት መሪ ቻክ ሹመር በረቂቅ ህጎቹ ላይ ማብራሪያ መስጠታቸው፣ ከኦክላሃማው ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ጋር ውይይት ማድረጋቸው፣ ለአሜሪካ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ሕጎቹ የሚያደርሱትን ጉዳት የተመለከተ ደብዳቤ ማስገባታቸው በተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ለማከናወን በዕቅድ መያዛቸው በዳያስፖራው እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ናቸው፡፡ ሁለቱም ረቂቅ ህጎች ጸድቀው ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተመርቶ ሲፈርሙበት ህግ ሆኖ የሚወጣ በመሆኑ፤ በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ህግ ሆነው እንዳይወጡ የኮንግረስ አባላትንና ሴናተሮችን በማነጋገር እንዲሁም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻዎችን እያደረጉ ይገኛሉ።
ህጉ ከታሰበበት ዓላማ ውጪ በጎንዮሽ በህዝብ፣ በሀገር ደህንነት፣ እና ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አስከፊ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በህጉ ከተደነገጉት ሃሳቦች በላይ እኛ እንደ ህዝብ እና ዜጋ የምንወስደው እርምጃ ይበልጥ ትርጉም ያለውና እጅግ ተፈላጊ ነው የሚሉ ሃሳቦችን የሚሰነዝሩም አልጠፉም፡፡ ለዚህም ነው ዶክተር ወሮታው በዛብህ አሁናዊ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባትና ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ መነሳት ይገባል የሚሉት፡፡
“ከምዕራባዊያን ማዕቀብና ጫና ይልቅ ሙስና፣ ዘረኝነት፣ ቢሮክራሲ ያስፈራኛል” የሚሉት ዶክተር ወሮታው በዛብህ የውጭውን ጫና እንደለውጥ መነሻ ምክንያት በማድረግ በቁጭት መነሳት፣ የውጭ አምላኪነትን መቀነስ፣ ችግር ፈች ትውልድ ማፍራት ላይ ማተኮር እንደሚገባም ጨምረው ምክረ-ሃሳባቸውን የለገሱት።
ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው እየተሰነዘሩ ያሉ ጫናዎችን ለመመከትና የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጋፋት በግልጽም ሆነ በስውር የሚደረጉ የጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል፤ አብሮነትን ከሚሸረሽሩ ጥቃቅን አጀንዳዎች መራቅ፣ ሀገራዊ አንድነትን በሚያጎለብቱ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ የሀገር ውስጥ ቁጠባን ማጠናከር፣ የስራ እና የአኗኗር ዘይቤን መቀየር እና ማሻሻል፣ ከጥንት ጀምሮ ሲሸጋገር የመጣውን ርስ በራስ የመረዳዳት ባህልና እሴት ማጎልበት፣ የመንግስት አገልግሎቶችን በፍጥነትም፣ በጥራትም ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ፍጆታን በራስ አቅም ማምረት የሚያስችል አቅም እና ቴክኖሎጂን አሟጦ መጠቀም፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ምርት መተካት ላይ ማተኮር፣ በብዛትም በማቅረብ የህዝቡን ፈጣንና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት የማግኘት መብት ማረጋገጥ፣ በንግድ ዘርፉ እና በመንግስት መዋቅር ጭምር የተንሰራፋውን ሙስና ለመግታት ህዝቡን ባሳተፈ መንገድ መንግስታዊ ቁርጠኝነት የታከለበት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኑነቶችን ማጠናከር፣ የቴክኖሎጂ የፈጠራ እንዲሁም የምርምር ስራዎችን የማበልጸግ እንቅስቃሴዎችን ማበረታታት፣ የስራ ዕድል ፈጠራን ማስፋት እንዲሁም ሀብትን በቁጠባ መጠቀም ችግሩን ለመቋቋም መልካም ስልቶች መሆናቸውን የዘርፉ ምሁራን ያስገነዝባሉ፡፡