በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት የደረሰባቸው ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው ሥራ እንዲጀምሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት የደረሰባቸው ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው ሥራ እንዲጀምሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 23/2014(ኢዜአ) በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው ሥራ እንዲጀምሩ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ፓርኩ ገለጸ።።
አሸባሪው ህወሃት ወረራ በመፈፀም የጥቃት ኢላማ ካደረጋቸው መካከል የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንዱ ነው።
ከፓርኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም ፓርኩ ላይ ዘረፋና ውድመት የተፈጸመ ሲሆን በዚህም ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ውድመት ተፈጽሟል።
የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑ ኩባንያዎች መካከል ማይክል ኮርስ የሚል ስያሜ የተሰጠው የሴቶች የእጅ ቦርሳ የሚያመርተው የደቡብ ኮሪያው ፑን ኩክ ኩባንያ አንዱ ነው።
የኩባንያው የሰው ኃይልና ጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊ ያሬድ እንዳላማው ፓርኩን ለጎበኙ ጋዜጠኞች እንዳብራሩት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ኩባንያው ምርቱን በጥሩ ሁኔታ እየላከ ነበር።
በዚህም በስሩ እስከ 1 ሺህ 16 ሰራተኞች እንደነበሩ አስታውሰው ከጦርነቱ በኋላ ግን ብዙ ጉዳት አስተናግደናል ነው ያሉት።
አሸባሪው ኃይል የኩባንያውን ተሽከርካሪዎች፣መለዋወጫዎች እና አንሺና ጫኚ መሳሪያዎች ዘረፋና ውድመት እንዳደረሰ ጠቁመው በዚህም ኩባንያው እስከ 400 ሺህ ዶላር ኪራሳ እንደደረሰበት አብራርተዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ኩባንያው ለሁለት ወር ያህል ሥራ ማቆሙን የተናገሩት ኃላፊው አሁን ላይ መልሶ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ተሟልተው ወደ ሥራ ተመልሰናል ብለዋል።
ኩባንያው አሁን ላይ ከጦርነቱ በፊት የቀረበለትን ትዕዛዝ ብቻ እያመረተ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ያሬድ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ትዕዛዞች መሰረዛቸውን አስታውቀዋል።
ኩባንያው 95 በመቶ የሚሆነውን ምርት ወደ አሜሪካ ይልክ እንደነበር የገለጹት ኃላፊው ኢትዮጵያ ከአጎዋ እድል ተጠቃሚ እንዳትሆን ማዕቀብ መጣሉ ትልቅ ተጽእኖ ፈጥሮብናል ነው ያሉት።
በፓርኩ በጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ላይ የተሰማራው የትራይ ባስ ብሪጅ ቴክስ ኢትዮ ኩባንያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ማሞ በበኩላቸው ኩባንያው በፊት የነበሩ ሰራተኞችን በመመለስ ወደ ምርት መመለሱን ተናግረዋል።
እንዲያም ሆኖ የገበያ እጥረት እየገጠመን ነው ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ በዚህ ላይ ድጋፍ እንሻለን ብለዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ያስተናገዱ ኩባንያዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ በመንግሥት በኩል የሚሰጠው ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ሰኢድ በበኩላቸው ፓርኩ ከደረሰበት ውድመት አገግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ ለመመለስ ርብርብ ተደርጓል።
በተለይም ጦርነት ከነበረበት አካባቢ ውጪ የነበሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸውን ጠቁመው ይህም ፓርኩ ተሎ ወደ ሥራ እንዲመለስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
ከጠርነቱ በኋላ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል።
በፓርኩ ውስጥ የተሰማሩ ኩባንያዎች በምርት ላይ እንዲቆዩ ድጋፎች እየተደረጉ ነው።
አቶ አህመድ እንደሚሉት ኩባንያዎች የሰባት ወር የሼድ ኪራይ እንዳይከፍሉ መደረጉ አመልክተው ይህም ከሚሰጡ ድጋፎች መካከል አንዱ ነው።
በተለይም ኩባንያዎች የሚያስፈልጋቸው የቴክኒክ እገዛዎች በፓርኩ በኩል እየቀረቡ መሆኑም አክለዋል።
ኩባንያዎች የገጠማቸውን የገበያ መቀዛቀዝ ችግር ለመፍታት የገበያ መዳረሻ ቦታዎችን የማስፋት ሥራም በቀጣይ በትኩረት የሚሰራ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ የአጎዋ ተጽዕኖ ለማካካስ ምርቶችን ከአሜሪካ ውጭ ወደ አውሮፓ አገራት ለመላክ ኩባንያዎች የሙከራ ምርት በማምረት ላይ ናቸው።
ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2017 በ93 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።