ኢትዮጵያ በሁለት ታላላቅ ጉዳዮች የገነነችበት ሳምንት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሁለት ታላላቅ ጉዳዮች የገነነችበት ሳምንት

ምንይችል አለማየሁ (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሳምንት ሁለት አንኳር ጉዳዮችን አስተናግዳለች። አንደኛው በአህጉረ አፍሪካ ብዙም ያልተለመደና ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የአሁኑ ትውልድ ላሊበላን ከፈለፈሉና አክሱምን ያቆሙ የቀደምት አያቶቹን ወኔ ታጥቆ እየገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰባተኛ ዓመት ክብረ በዓል ነው። ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እዚህም እዚያም "ብቅ እልም" በሚሉ አለመረጋጋቶች ስትታመስ መቆየቷ እሙን ነው። አነዚህ አለመረጋጋቶች በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በስፋት ተንጸባርቀዋል። በአንዳንድ አካባቢዎችም የተፈጠሩት አለመረጋጋቶች ወደ ለየላቸው ግጭቶች ተሸጋግረው ከንብረት ማውደም ባለፈ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ቀጥፈዋል። የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እነዚህን አለመረጋጋቶች እንደጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ቀድመው ባስቀመጡት አጀንዳ ልክ በሚፈልጉት ሁኔታ ተንትነውታል፤ "ኢትዮጵያ አበቃላት" እስከማለት የደረሱ መገናኛ ብዙሃን ነበሩ። በተለይ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን በዚህ ፕሮፓጋንዳ ተጠምደው እንደነበረ አይዘነጋም። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ስለ አለመረጋጋቱ ሲዘግቡት የነበረውን መረጃ ለህዝብ ይፋ እስከ ማድረግ መድረሱም ይታወሳል። ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ማንነታቸው በቅጡ የማይታወቅ፤ ከየትኛው ጎራ መሆናቸው የማይለይ፤ ነገር ግን የነበረውን አለመረጋጋት ወደ ደም አፋሳሽ እልቂት ለመቀየር የተለያዩ ምስሎችን በማስደገፍ (በአመዛኙ የተቀነባባሩ) "ግፋ በለው" ሲሉ ከርመዋል። ይህ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ የሚለው አለመረጋጋት ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው ሲኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች እርስ በርስ እንዲጠራጠሩ ከማድረጉም በላይ፤ አገሪቷ በታሪኳ አይታው በማታውቀው መንገድ በርካታ ዜጎችን ከሞቀ ቀያቸው አፈናቅሏል። በሱማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን የዜጎች መፈናቀል ለአብነት ማንሳት ይቻላል። መንግስት በበኩሉ እነዚህ አለመረጋጋቶች ምንጫቸው ብሶቶች ናቸው። አመራር አባላት በሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመዘፈቃቸው የተፈጠረ ነው ሲል በትዕይንተ መስኮት ቀርቦ በተደጋጋሚ ተናግሯል። አገሪቷን የሚመራው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ከአለመረጋጋቶቹ ማግስት "ህዝብ የጣለብኝን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት" በሚል በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ የጀመረ ሲሆን፤ የተሃድሶ ሂደቱንም በየጊዜው እየገመገመ፣ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን በተደጋጋሚ ይፋ አድርጓል። የወቅቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከህዝብ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሰላም ለመፍጠር ሲልም በመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። አዋጁ በተቀመጠለት ጊዜ ገቢራዊ ሆኖ የተነሳ ሲሆን፤ በእነዚህ ጊዜያት መንግስት ህዝቤን በድላችኋል ያላቸውን አመራር አባላት ተጠያቂ ከማድረግ በተጨማሪ አዲስ ካቢኔ እስከማዋቀር የደረሰ ውሳኔ አሳልፏል። እንዲህ እንዲህ እያለ የመጣው የኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ ከመሻሻል ወደ ባሰ ክስተት በመሄዱ እና በአንዳንድ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች በመፈጠራቸው አገሪቷ ድጋሚ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር እንድትወድቅ ዳርጓታል። የኢህአዴግ አራቱ እህት ድርጅቶች ችግሩን ከስር መሰረቱ መፍታትን ያለመ ግምገማ መጀመሪያ በተናጥል፤ ከዚያ በጋራ ያካሄዱ ሲሆን፤ ከግምገማው በኋላ የድርጅቶቹ ሊቃነ መናብርት እርስ በርስ የተፈጠረባቸውን መጠራጠር እንደፈቱ፤ ከስልጣን በፊት ለአገርና ህዝብ የሚል አቋም እንደያዙና ኪራይ ሰብሳቢነትን በቁርጠኝነት ለመታገል እንደተነሱ መግለጫ ሰጡ። ከመግለጫው ጥቂት ቀናቶች በኋላ የኢህአዴግና ደኢህዴን ሊቀመንበር እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ "ለወቅታዊ ችግሮች የመፍትሄ አካል ለመሆን" በማለት የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ በይፋ አቀረቡ። በእርሳቸው የመልቀቂያ ጥያቄም የተለያዩ አመለካከቶች ተንጸባርቀዋል። አንዳንዶቹ ማን ይተካቸዋል ሲሉ፤ ሌሎች በተለይ ከአገር ውጭ የሚኖሩ የተለያዩ አካላት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) "አብቅቶለታል፤ መንግስት ሊፈርስ ነው" ሲሉ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን በመጠቀም ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም ምክር ቤቱ ቀናቶችን የፈጀ ግምገማ ካካሄደ በኋላ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጥያቄ ተቀብሎ የኦህዴድ ሊቀመንበር የሆኑትን ዶክተር አብይ አህመድን የግንባሩ ሊቀ መንበር አድርጎ መሾሙን አስታወቀ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በዚህ ሳምንት መባቻ ባካሄደው ስብሰባ አዲሱን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድን የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰየመ። የስልጣን ሽግግሩን አምባሳደሮች እንዴት ገለጹት? በኢትዮጵያ የተካሄደው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ከኢትዮጵያውያን እስከ ውጭ አገሮች ዲፕሎማቶች አድናቆት ተችሮታል። በተለይ የሽግግሩን ሂደት በምክር ቤቱ ሲከታተሉ የነበሩ የተለያየ አገር አምባሳደሮች ሁኔታው በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እንደነበር ሲገልጹ ተስተውለዋል። ሽግግሩ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ የሚሆንና አገሪቷ ለገባችበት ወቅታዊ ችግር ትክክለኛ መፍትሄ እንደሆነ የተናገሩም ነበሩ። በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ቫነት ሉስድሬች አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካለፉት ስህተቶች ተምረው ለአገሪቷ ጥሩ ነገር ይዘው እንደሚመጡ እንደሚያምኑ ሲገልጹ፤ በኢትዮጵያ የቬንዙዌላ አምባሳደር ሊዊስ ማሪኖ ማታ "ኢትዮጵያ የየትኛውንም አገር ጣልቃ ገብነት ሳትፈልግ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል ያሳየችበት ሂደት" እንደሆነ ተናግረዋል። "ሰላማዊ የስልጣን ሽግግሩ በአገሪቷ ዴሞክራሲ አዲስ ምዕራፍ እንደከፈተ" የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የሲሪላንካ አምባሳደር ሲመት ዳስናይክ ናቸው። በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሞኒራል ኢስላም በበኩላቸው "ሰላማዊ ሽግግሩ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው" ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የስልጣን ሽግግሩን አስመልክቶ በድረ-ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት ዶክተር አብይ አህመድን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መሾሙ የሚያስደስትና በአዎንታዊ መልኩ የሚቀበሉት እንደሆነና አሜሪካም ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በቅንጅት እንደምትሰራ መግለጫው አትቷል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት መባቻ አንድ መሪ በህይወት እያለ፤ አዲሱ የቀደመውን አሞግሶ፤ የቀደመው ደግሞ አዲሱን ተሿሚ "ህዝቤን አደራ" በማለት ህገ መንግስትና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረክቦ፤ ለበርካታ አፍሪካውያን እንደ ህልም የሚቆጠር የነበረና በአህጉሪቷ ባልተለመደ መልኩ መሪዎች ተቃቅፈው ስልጣን ሲረካከቡ ለዓለም አሳይታለች። ይህ ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራና ላብ ያረፈበት፤ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም ብቻ እየገነቡ ያሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተበሰረበትን ሰባተኛ ዓመት ልደት አክብራለች። የግድቡ ግንባታ አሁን ባለበት ደረጃ 65 በመቶ ደርሷል፤ በዚህ ዓመት መጨረሻም በሁለት ዪኒቶች ኃይል ማመንጨት በመጀመር ኢትዮጵያውያንን እራት የማብላቱን ተግባር አሃዱ እንደሚል ይጠበቃል። ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ግድቡ እዚህ እንዲደርስ እስካሁን ባሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ 10 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማዋጣታቸውን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በአጠቃላይ ሳምንቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት የሄዱበት ርቀት የታየበትና ሁሉም በአንድነት ከተባበረ የሚያቅታቸው ነገር እንደሌለ ለዓለም ያሳዩበት ነበር። ወትሮም ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት እና የሰው ዘር ሁሉ መገኛ መሆኗን ለዓለም በምታሳይበት ጊዜ የጨዋና ታላቅ ትውልዶች ቅብብሎሽ ሁባሬነቷን ከሚታስመሰክርበት አጋጣሚዎች አንዱ የሳምንቱ ታላላቅ ሁነቶች ዓይነት ነውና የአገራችንን ህዳሴ በተግባር እናስመስክር። ሰናይ ጊዜ!