በኢጋድ የብሉ ኢኮኖሚን የሚያስተባብሩ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢጋድ የብሉ ኢኮኖሚን የሚያስተባብሩ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
መጋቢት 23 ቀን 2014 ( ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የ'ብሉ ኢኮኖሚ' ን የሚያስተባብሩ ሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
‘ብሉ ኢኮኖሚ’ የውቅያኖስ፣ የሀይቅና የባህር ሀብቶችን እንዲሁም ወደቦችን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋልን ማዕከል ያደረገ ነው።
በስብሰባው የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስን ጨምሮ የአባል አገራት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።
ሚኒስትሮቹ ኢጋድ ለቀጣይ 5 አመታት ተግባራዊ እንዲሆን ያዘጋጀውን የኢጋድ 'ብሉ ኢኮኖሚ' ስትራቴጂ ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአፍሪካ የአየር ንብረት ተጽዕኖን በመቋቋም ዘላቂ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት 'ብሉ ኢኮኖሚ' ያለውን አስተዋጽኦ አስረድተዋል።
በዝናብ ላይ የተመሰረተውን የግብርና ስራ ለመደገፍ፣ የስራ እድል ለመፍጠር፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ መካከል ዘርዝረዋል።
"ብሉ ኢኮኖሚ" በአሳ ልማት በኩል ያለውን አቅም በመጠቀም ለምግብ ዋስትና መጠቀም እንደሚቻል ጨምረዋል።
ለሃይል ማመንጫ፣ ትራንስፖርትና ሌሎች በመጠቀም ዘርፉ አካታችና ዘላቂ ልማት ለማምጣት ያለውን አስተዋጽኦ ዶክተር ወርቅነህ ዘርዝረዋል።