ኢሕአፓ "ኤችአር 6600" እና "ኤስ 3199" ረቂቅ ሕጎችን በጽኑ ይቃወማል

92

መጋቢት 22/2014(ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕልውና የሚፈታተኑና አቅመ-ቢስ መንግስት ለመመስረት ዓላማ ያላቸውን "ኤችአር 6600" እና "ኤስ 3199" ረቂቅ ሕጎችን በጽኑ እንደሚቃወም ገለጸ፡፡

በውጭ አገራት የሚኖሩ አባላትና ደጋፊዎቹ ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ በሚመለከታቸው አካላት ላይ ጫና እንዲያደርጉ መመሪያ ማስተላለፉንም አስታውቋል።

ኤች አር 6600 ወይም "ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት" ቶም ማሊኖውስኪ በተባለ በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ዋና አርቃቂነት እና በበያንግ ኪም፣ ግሪጎሪ ሚክስ፣ ዴቪድ ሲሲሊን፣ ብራድ ሼርማን እና ማይክል ማካውል በተባሉ አባላት ደጋፊነት የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ነው።

ረቂቅ ህጉም ኢትዮጵያን በጽኑ የሚጎዳ ሐሳቦችን የያዘ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ- አሜሪካ ግንኙነትን የሚጎዳና ኢትዮጵያን ለከፋ ችግር የሚዳርግ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው መግለጹ ይታወቃል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ መጋቢ ብሉይ አብርሃም ኅይማኖት  ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሁለቱ ረቂቅ ሕጎች የኢትዮጵያን ህልውና የሚጎዳና የአገራቱን ሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያሻክሩ ናቸው፡፡

ረቂቅ ሕጎቹ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት የሚያሽመደምዱ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማያስከብር አቅመ-ቢስ መንግስት እንዲኖር እና ኢትዮጵያን መገነጣጠል የሚሹ አሸባሪ ኃይሎች እንዲያንሰራሩ ዕድል የሚሰጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን አንድነት የሚሹ አካላትን የሚያፍን እንዲሁም የኢትዮጵያን ህዝብ በዘላቂነት ለችግር የሚያጋልጥ ሰነድ እንደሆነም  ጨምረው ገልጸዋል።

በተለይም በኢኮኖሚ ረገድ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የልማት ፕሮጀክቶች እንዳትፈጽም የውጭ ድጋፍና ብድርን የሚያግድና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ድጋፍ የሚከለክል እንደሆነም እንዲሁ፡፡

አንዳንድ አካላት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን አደገኛ ረቂቅ ህግ ሲደግፉ እየተሰተዋለ መሆኑን አንስተው፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ህልውና የሚፈታተን ሕግ መደገፍ እጅግ የተሳሳተ አካሄድ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

"የኢትዮጵያ ህዝብ ለችግር ተጋልጦ እኔ ስልጣን ላይ ልውጣ የሚል አካሄድ ተቀባይነት የለውም " ያሉት ኃላፊው፤ ከዚህ አኳያ ኢሕአፓ ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል የሚሰሩ ኃይሎችን በጽኑ እንደሚቃወም አብራርተዋል፡፡

ኢሕአፓ ሥልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድሮ መያዝ እንጂ ደካማ መንግስት እንዲኖር ከጠላት ጋር መተባበር አይፈልግም ነው ያሉት።

ገዥው ፓርቲን ወይም መንግስትን ስለጠሉ ብቻ አገርና ህዝብን በሚጎዳ መልኩ ከጠላት ጋር መሰለፍ የመረጡ አካላት አካሄዳቸውን ማጤን እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።

ከዚህ አኳያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አገርን ከችግር ለመታደግ በሚችሉት ሁሉ ረቂቅ አዋጆቹ እንዳይጸድቁ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ጠይቀዋል፡፡

ፓርቲው በመላው ዓለም አባላትና ደጋፊዎች እንዳሉት ገልፀው፤ አባላትና ደጋፊዎች ይህ ሰነድ እንዳይጸድቅ በሚችሉት መንገድ ሁሉ ጫና እንዲያደርጉ መመሪያ እንዳስተላለፈ ተናግረዋል፡፡

ሌሎች በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያንም ረቂቅ አዋጆቹ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት በመገንዘብ እንዳይጸድቁ ሊታገሉ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግስት በውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን አስተባብሮ በጉዳዩ ላይ መሥራት እንዳለበትና ዳያስፖራው አንድነቱን ጠብቆ ለአገሩ ያለውን አጋርነት በተግባር ማሳየት እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም