ቀጥታ፡

ለአምራች ኢንዱስትሪ እድገት ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን ለማስተካከል የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረጉ ነው

መጋቢት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ )ለአምራች ኢንዱስትሪ እድገት ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን ለማስተካከል የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።

"ብሩህ ማይንድ" የተሰኘ በቢዝነስ ሃሳቦች ዙሪያ የሚያማክር ድርጅት ባዘጋጀው ወርሃዊ የምክክር መድረክ ላይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ ምክክር ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የሥራ እድል ፈጠራ በሚፈለገው ደረጃ ለማስፋት የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ በዚህ ጊዜ  እንደገለፁት፤ የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት ከለውጡ በኋላ በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎችና ዘርፉን የማዘመን ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ከማሻሻያዎቹ መካከል የብድር አቅርቦት ማመቻቸት፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ መሥጠትን ጨምሮ ለዘርፉ ማነቆ የነበሩ አሰራሮችን በማሻሻል ረገድ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

በተለይ ከፖሊሲ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙ ማነቆዎችን ለማስተካከል በ1994 የወጣውን የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ለማሻሻል ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሃላፊነቱን ወስዶ እየሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በአምራች ኢንዱስትሪ የነበረው የፖሊሲ ማዕቀፍ በውጭ አገር ግብዓት ላይ መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቅ በመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪውን የማያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ለአምራች ኢንዱስትሪ እድገት ማነቆ የሆኑ እንዲህ ያሉ አሰራሮችን ለማስተካከል የፖሊሲ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

እየተሻሻለ ያለው የፖሊሲ ማዕቀፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ታዋቂ አማካሪዎች እየተሳተፉበት ያለና በዚህ ዓመት መጨረሻ ተጠናቆ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ፖሊሲው ተግባራዊ ሲሆን አሁን ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ምህዳሩን በማስፋት ዘርፉን የሚያዘምን እንደሆነ ገልጸው በዚህ ዓመት ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም