ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ወጣቶችን ያማከለ የመፍትሔ ሂደት ወሳኝ ነው -ምሁራን

መጋቢት 22/2014/ኢዜአ/  አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ወጣቶችን ያማከለ የውይይትና የመፍትሔ ሂደት ወሳኝ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ወጣት የህብረተሰብ ክፍል በሚገባ ያሳተፈ አካታች ወይይት መደረግ እንዳለበት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን አመልክተዋል።

በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህርት የሆኑት ኦርጂ ቢሶ እንደ አገር የሚታዩ ችግሮችን ለመለየትና መፍትሄ ለመስጠት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ወሳኝ ሚና ቢኖራቸውም የወጣቱ ሚና የማይተካ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ያሻዋል ብለዋል።

አካታች ውይይት ለለውጥ ስራዎች ግብአት መሆኑን በመጠቆም ከግማሽ ባላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ወጣት በመሆኑ በአገራዊ ምክክሩ ወጣቶችን ዋና ማዕከል ማድረግ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አረዳድ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ጋሻው አይፈራም በበኩላቸው አገር በሃሳብ እንደሚገነባ ገልጸው አገርን ከሚገነቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንባር ቀደሞቹ ወጣቶች ናቸው ብሏል።

ወጣቱ ያለውን የመለወጥ ፍላጎትና ጥያቄ  የሚያንጸባርቅበትና ሀሳቡን የሚገልጽበት ምቹ ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዘመናት የኢትዮጵያ ወጣቶች ለለውጥ ሲታገሉ መቆየታቸውን አመላክተው ወጣቱ በርካታ አገራዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ ትልቅ ሚና መጫወቱን አክለዋል።

ወጣቱ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ከሚመዘገቡ አገራዊ ለውጦች ተጠቃሚ እንዲሆንም አገራዊ ምክከሩ የወጣቶችን ድምጽ በማካተት ሊከናወን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

አገራዊ ምክክሩ ሐሳብን በግድ መጫንን፣ ጦር መማዘዝን፣ ሕዝብን እና ሀገርን አደጋ ላይ መጣልን ከመሳሰሉ አደጋዎች የሚያድንና በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ በልዩ ትኩረት ሊሳተፍበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም