ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ስፖርት ክለብ ከ8 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ በነገው እለት ጨዋታውን ያደርጋል

መጋቢት 22/2014/ኢዜአ/  የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ስፖርት ክለብ ከ8 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ በነገው እለት ጨዋታውን ያደርጋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 30 ክለቦች በሶስት ምድብ ተከፍለው እየተጫወቱ ይገኛሉ።

በምድብ "ሐ"  ከተደለደሉት ክለቦች ምድቡን በ37 ነጥብ እየመራ ያለው የኢትዮጵያ መድን በነገው እለት ከደቡብ ፖሊስ ጋር  በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስቴዲዬም የሚጫወት ይሆናል።

በተመሳሳይ በዚሁ ምድብ የሚገኘውና በ36 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ነቀምት ከተማ ከየካ ክፍለ ከተማ በሐዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ይጫወታል።

ኢትዮጵያ መድን በጫወታው ማሸነፍ ከቻለ የነቀምትን ውጤት ሳይጠብቅ ፕሪምየር ሊጉን የሚቀላቀል ይሆናል።

ነቀምት ከተማ  ደግሞ ፕሪምየር ሊጉን ለመቀላቀል ተጋጣሚውን የካ ክፍለ ከተማን ማሸነፍ እና የመድንን  ውጤት መጠበቅ ግድ ይለዋል፡፡

ይህ ጨዋታ በተመሳሳይ ሰዓት ነገ ከቀኑ 9:00 ሰዓት የሚደረግ ይሆናል።

በምድብ "ለ"  ደግሞ ለገጣፎ ለገዳዲ በ33  ነጥብ ሲመራ፤  ቤንቺ ማጂ  ቡና  በ30 ነጥብ በሁለተኝነት እየተከተለ ይገኛል፡፡

ሁለቱ ክለቦች ፕሪምየር ሊጉን ለመቀላቀል ይፎካከራሉ፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ "ሀ" ከተደለደሉት ውስጥ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አንድ ጨዋታ እየቀረው ፕሪምየር ሊጉን  መቀላቀል ያረጋገጠ  ክለብ ነው።

የከፍተኛ ሊጉ ከሶስቱም  ምድብ አንደኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ክለቦች  በቀጥታ ፕሪምየር ሊጉን  የሚቀላቀሉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም