ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን የአገርን አንድነትና የሕዝብን አብሮነት የሚያጠናክሩ እሴቶችን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል

መጋቢት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን የአገርን አንድነትና የሕዝብን አብሮነት የሚያጠናክሩ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ለማጠናከር መሥራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አሳሰበ።

ባለሥልጣኑ የሃይማኖት ብሮድካስት ረቂቅ መመሪያን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙኃን ለህዝብ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን በማቅረብ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።

ጎን ለጎንም በሚሰሯቸው ሥራዎች ለአገሪቱ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለመልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መጎልበት የበኩላቸውን ገንቢ ሚና መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃንም ለተከታዮቻቸው ከሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጎን ለጎን የሕዝብን አንድነትና አብሮነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በተለይም የሁሉም ሃይማኖቶች የጋራ እሴት የሆኑ እንደ አብሮነት፣ መረዳዳት፣ የሰላምና ፍቅር እሴቶች  በኅብረተሰቡ ውስጥ ለማስረፅ ከፍተኛ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲና ሕጎች መሰረት የሃይማኖት ተቋማት ብሮድካስት እንዲያቋቁሙ ሕጋዊ ዕውቅናና ፈቃድ እንዳያገኙ ተከልክለው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ሃይማኖታዊ አስተምህሮ መርሃግብሮችን ለማስተላለፍና ለመከታተል ፍላጎት መኖሩን በመገንዘብ የሃይማኖት ብሮድካስት አገልግሎታቸውን በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎም የሚዲያ ዘርፍ አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግ የሪፎርም ጥናት፣ የፖሊሲ ዝግጅትና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በማሻሻል ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

ከእነዚህ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲና አዋጅ ማሻሻያ ከተደረገባቸው አንዱ የሃይማኖት ብሮድካስተሮች በሕግና ዕውቅና አግኝተው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ  ከ50 በላይ የሚሆኑ የሃይማኖት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተለያዩ የሳተላይት ሥርጭት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

እነዚህ ጣቢያዎች ሃይማኖታዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ለተከታዮቻቸው አማራጭ ዘዴ በመሆን እያገለገሉ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአንጻሩ፤ ጥቂት የሚባሉ የሃይማኖት የመገናኛ ብዙኃን በሚያሰራጯቸው ኃላፊነት የጎደላቸው ዘገባዎችም ከኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ቅሬታዎቹም ከሕግ፣ ከሞራልና ከጤና ጋር የሚቃረኑ ንግግሮችን በማሰራጨት ሌሎች ሃይማኖቶችን የመንቀፍ፣ ራስን ከፖለቲካ ያለማራቅ ዝንባሌ እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

በመሆኑም የሃይማኖት የመገናኛ ብዙኃን ለአገራችን አንድነት፣ ለሕዝብ መፋቀር፣ አብሮነት፣ መረዳዳት፣ ሰላምና መሰል በጎ ሃይማኖታዊ እሴቶችን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

ከመጋቢት 23 ቀን 2014 ጀምሮም ለነባርና አዳዲስ ሃይማኖት ተቋማት የቴሌቪዥን አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ መስጠት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም