ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ‘ኤችአር 6600’ ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ተወካዮቻቸው ላይ ጠንካራ ግፊት ማድረግ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ‘ኤችአር 6600’ ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ተወካዮቻቸው ላይ ጠንካራ ግፊት ማድረግ አለባቸው
መጋቢት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ ተወካዮቻቸው ላይ ጠንካራ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ተናገረች።
የረቂቅ ሕጎቹ አርቃቂዎች የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የማያሳስባቸው ናቸውም ብላለች።
‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም 'ኤችአር 6600' በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት በኮንግረሱ የተዘጋጀ ረቂቅ ሕግ ነው።
የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ በአሜሪካ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ (ኒው ጀርዚ) ዋና አርቃቂነት፣ በሴናተር ጀምስ ሪስች (ኢዳሆ)፣ በሴናተር ክሪስ ኩንስ (ዴልዌር) እና በሴናተር ቶም ቲሊስ (ኖርዝ ካሮላይና) ደጋፊነት የተዘጋጀ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ሁለቱ ረቂቅ ሕጎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በብዙ መልክ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ላይ የሚያደርስ መሆኑን ለኢዜአ ገልጻለች።
ሕጎቹ አሜሪካ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጫና በማድረግ ኢትዮጵያ ብድርና ሌሎች ድጋፎች ከእነዚህ ተቋማት እንዳታገኝና እንድትገለል እንደሚያደርጋት ጠቁማለች።
ያም ብቻ ሳይሆን ረቂቅ ሕጉ ከጸደቀ የአሜሪካ አስፈጻሚው አካል የሕጉን አንቀጾች በብዙ መልኩ እንዲተረጉም እድል የሚሰጥ አደገኛ ረቂቅ ሕግ መሆኑን ነው ያነሳችው።
የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ይልቅ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንደሚያደርስና የኢትዮጵያ አሁን የጀመረችው የሰላም ሂደቱ ላይ ተጽእኖያሳድራል ብላለች።
ረቂቅ ሕጉ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ “በሐሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግር ስም” ኢትዮጵያን የሚደግፉ ድምጾችን በማፈን ለአገሩ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ የማስቆም ግብ እንዳለውም ገልጻለች።
በጦርነቱ የሰብዓዊ ጥሰትና ወንጀልን የሚያጣራ ነጻና ገለልተኛ መርማሪ ቡድን መቋቋም እንዳለበት በሕግ ውስጥ መካተቱን ጠቅሳ ይህም አግባብ አለመሆኑን ነው ያነሳችው።
ለዚህም ተአማኒ የሆነ አጣሪ የመመደብ መብት ያላት ኢትዮጵያ መሆኗን በመጠቆም።
“ረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያውያን ለእናንተ የተሻለ እናውቅላችኋላን፤ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ለማስከበር እኛ እናስጠብቅላችኋለን” የሚል አንድምታ እንዳለው ተናግራለች።
የረቂቅ ሕጎቹ አርቃቂዎች የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የማያሳስባቸውና ሕጎቹ ቢጸድቁ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ግድ እንደማይሰጣቸው መሆኑንም ጠቅሳለች።
ሕጎቹ የተጻፉት የሕወሓት ደጋፊዎች ለተወሰኑ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች በከፈሉት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ መሆኑን ተናግራለች።
ረቂቅ ሕጎቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምን ለማምጣት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ያላካተተና ለሰላም እንቅፋት የሆነውን ሕወሓት የሚደግፉ መሆኑንም እንዲሁ።
‘ኤችአር 6600’ ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጽድቁ በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ የሲቪክ ተቋማት እንዲሁም የኢትዮጵያና ኤርትራ ዳያስፖራዎች ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግራለች።
ዳያስፖራዎቹ በየአካባቢው ላሉት የኮንግረስና የሴኔት ተወካዮቻቸው ሕጎቹን እንደሚቃወሙትና እንደማይቀበሉት በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ መሆኑንም ነው የተናገረችው።
ያም ሆኖ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ እነዚሀ የሴኔትና የኮንግረስ ተወካዮቻቸው ላይ የሚያደርጉትን ግፊት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግራለች።
‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 የኮንግረስ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ውይይት በማድረግ “የኮንግረስ አባላት የኮንግረስ አፈ ጉባኤ በሚያቀርቡት ጥያቄ ድምጻቸውን በማሰማት አዎ ወይም አይደለም” በሚል ድምጽ የሚሰጡበት ሥርዓት (ቮይስ ቮት) አማካኝነት ረቂቅ ሕጉ በኮንግረሱ ይታይ ወይስ ማሻሻያ ይደረግበት? በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሕግ አውጪ ምክር ቤቱ መምራቱ የሚታወስ ነው።
የሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ በ‘ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ ከትናንት በስቲያ በመወያየት ለሴኔት ሙሉ ድምፅ እንዲቀርብ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።