በክልሉ የተሾሙት አዲስ ካቢኔዎች የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ መመለስ አለባቸው... አቶ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተሾሙት አዲስ ካቢኔዎች የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ መመለስ አለባቸው... አቶ አህመድ ሽዴ
ጅግጂጋ ነሀሴ 30/2010 በቅርቡ የተሾሙት አዲሶቹ የሶማሌ ክልል የካቢኔ አባላት የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለባቸው የፌዴራል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ አሳሰቡ፡፡ ሚኒስትሩ አዲስ ከተመረጡት የክልሉ ካቢኔ አባላት ጋር በጅግጂጋ ከተማ በተወያዩበት ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ተከስቶ የነበረው ችግር ተከትሎ የተፈጠረው የአመራር ክፍተት መልሶ ለማደረጀት መሪ ድርጅቱ እየሰራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተዋቀረው አዲሱ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተመረጡና ተገቢውን መንግስታዊ አገልግሎት በማቅረብ ለውጥ እንደሚያመጡ የታመነባቸው ናቸው፡፡ " ህዝብን ማገልገል ትልቅ ክብር ነው፤ የተረከባችሁት ኃላፊነት የህዝቡን መሰራታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት በቅንነት መስራት ይገባል" ብለዋል፡፡ አቶ አህመድ እንዳሉት በቅርቡ በክልሉ ተከስቶ የነበሩ የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በድጋሚ እንዳይከሰት አዲሱ የካቢኔ አባላት ሙስና፣ ጎሰኝነት እና አፍራሽ አስተሳሰቦችን አጥብቆ መታገል ይጠብቅባቸዋል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው ለአዲሶቹ የቢሮ ኃላፊዎች አርብቶ አደሩ ህዝብ በመንግስት ሊፈቱ የሚገቡ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ " የክልሉ አመራር ስልጣን የህዝብ ማገልገያ መሆኑን ተረድታችሁ ህዝቡን ማስቀደም አለባችሁ"ብለዋል፡፡ ከአዲሱ አመራር አካላት መካከል አቶ አደን ፋራህ በሰጡት አስተያየት የለውጥ እንቅስቃሴውን ከዳር ለማድረስ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመውጣት ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ሌላው የካቢኔ አባል አቶ መሀመድ ፋተሕ በበኩላቸው በክልሉ በፍትህ ዘርፍና የልማት ፕሮጅክቶች ላይ የሚፈፀመው ሙስና ለማስቀረት ቅድሚያ በመስጠት ስርዓት ለማስያዝ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የክልሉን መንግስት የሚመራው የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ ሊቀመንበር ናቸው፡፡